የሀገር ውስጥ ዜና

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

By Adimasu Aragawu

April 11, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ለ2018 ዓ.ም የትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ በመልዕክታቸው÷ መላው ሕዝበ ክርስቲያንና የሀገራችን ሕዝቦች፣ በመላው ዓለም የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወገኖች እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል።

የክርስትናችን መሠረት የሆነውን በዓል በአግባቡ የምናከብረው የክርስቶስን ተልዕኮ በአግባቡ በተረዳነው መጠን ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡

የክርስቶስ የትንሳኤው ምስጢር አንድን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የመላውን የሰው ልጅ ሕይወትን እንደሚመለከት የምንረዳው በወንጌልና በትንሣኤ የምሥራች መሆኑን ጠቅሰው÷ ስቃይና ክብር፣ ሞትና ትንሣኤ፣ ድካምና ኃይል በወንጌል ፍጻሜን ሲያገኙ የምናየው በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ነው ብለዋል፡፡

በዓሉን ስናከብር የጌታን ትንሣኤ ምስጢር ለመረዳት፣ ለመሳተፍ እና ለመኖር ያሉት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ÷ ከሁሉም በላይ ደግሞ የትንሣኤ በዓል የክርስቲያኖች የትንሣኤ ቀን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከመላው የሀገራችን ሕዝቦች ጋር በመተባበርና በአንድነት በመቆም መጥፎ ስራን ልንቃወም ይገባል ነው ያሉት፡፡

ፈጣሪ በሀገሪቱ የተፈጥሮ ጉዳት ላጋጠማቸው መፅናናትን፣ ለታመሙት ምህረትን፣ ላዘኑት መጽናናትን፣ ለታሰሩት መፈታት፣ ለተፈናቀሉ ወደ ቀያቸው መመለስን፣ ለተራቡና ለተጠሙ ምግብና ውሃን እንዲሰጥም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዓሉን ስናከብር ከችግረኞች፣ አስታዋሽ ከሌላቸው፣ በጎዳናና በየመጠለያ ቦታዎች ላይ ያሉ ወገኖቻችንን በማገዝና በመርዳት ማክበር ይገባል ሲሉም ማሳሰባቸውን ቤተክርስቲያኑ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡