የሀገር ውስጥ ዜና

ከንቲባ አዳነች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት አስረከቡ

By Melaku Gedif

April 11, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለሀገር ባለውለታዎች የመኖሪያ ቤት አስረክበዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ዘመኑን በዋጀ መልኩ ራሷን እያዘመነች ትገኛለች፡፡

የከተማዋን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት የሚመጥኑ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶች ባለፉት ዓመታት መገንባታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በዛሬው ዕለትም በቦሌ ክፍለ ከተማ በተገነባው ዘመናዊ ባለ አራት ወለል ሕንጻ ላይ 215 መኖሪያ ቤቶችን ከሙሉ የቤት ቁሳቁስና ከበዓል መዋያ ጋር ለነዋሪዎች ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡

ቤቶቹ በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር በጥቂት ወራት የተገነቡ ናቸው ያሉት ከንቲባዋ ÷ስንተባበርና በጋራ ስንቆም ትልልቅ ሥራዎችን መከወን እንችላለን ብለዋል፡፡

ለመኖሪያ ቤት ሕንጻው የኦሮሚያ ባንክ ከ80 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን ገልጸው ÷ ሌሎች በጎ ፈቃደኞች፣ ተቋማትና አመራሮች መሳተፋቸውን አመልክተዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች የትንሣኤ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ በፍቅር ራሱን እስከ መስቀል የሰጠበት እና በትንሣኤ የምሥራች የተበሰረበት ነው ሲሉ አውስተዋል።

በመሆኑም በዓሉን ስናከብር በትሳኤ ዓላማ እና ምሳሌነት መሰረት በታላቅ ፍቅር እና መተሳሰብ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

በዓሉ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ያለንን መተሳሰብ በተግባር የምንገልጽበት፣ አንዳችን ለሌላችን የደስታ፣ የሰላም እና የአብሮነት ምክንያት የምንሆንበት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

በአንዷለም ተስፋዬ