አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ለትንሳዔ በዓል ከሚከናወን የእንስሳት እርድ የሚገኙ ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ ማስወገድ ይገባል አለ የከተማ አስተዳደሩ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን።
የባለስልጣኑ ም/ሥራ አስኪያጅ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው እንዳሉት÷በአዲስ አበባ የተከናወነው የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት የከተማዋን የአፍሪካ መዲናነት የሚመጥን ነው፡፡
የከተማዋን ውበትና ምቹነት እንዲሁም የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ይበልጥ ለማሳደግም የተጠናከረ የደንብ ማስከበር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች ላይ የሚስተዋሉ የደንብ መተላለፍ ተግባራትን ለመከላከል በቁርጠኝነት እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በመሬት ወረራ፣ በሕገ ወጥ ንግድ፣ በአዋኪ ተግባራት፣ በሕገ ወጥ እርድና ሌሎች ተግባራት ላይ አስፈላጊው ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አቶ ንጋቱ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡
ከትንሳኤ በዓል ጋር ተያይዞ በመዲናዋ የሚከናወን ሕገ ወጥ እርድና ተገቢ ያልሆነ የእንስሳት ማጓጓዝ ሒደትን ለመቆጣጠር ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል፡፡
ጤንነቱ የተረጋገጠ የቁም እንስሳት እርድ ማከናውን እንደሚገባ ጠቁመው ÷ በመዲናዋ የሚከናወን ሕገ ወጥ የእንስሳት እርድን ለመከላከል እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡
ሕብረተሰቡ ለትንሳኤ በዓል የእርድ እንስሳትን በሚያጓጉዝበት ወቅት የመዲናዋ የኮሪደር ልማትና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
በተጨማሪም በበዓሉ ከሚከናወን የእንስሳት እርድ የሚገኙ ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ ማስወገድ እንደሚገባ ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡
በእርድ ወቅት የሚገኙ ደረቅ እና ፈሳሽ ተረፈ ምርቶችን በመዲናዋ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት በተገቢ መልኩ ማስወገድ እንደሚገባ ም/ሥራ አስኪያጁ አሳስበዋል፡፡