የሀገር ውስጥ ዜና

ድርጅቱ ለትንሳኤ በዓል ከ4 ሺህ በላይ የእርድ እንስሳት አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁ አለ

By Melaku Gedif

April 11, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለትንሳዔ በዓል ከ4 ሺህ በላይ የእርድ እንስሳት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት አጠናቅቄያለሁ አለ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት፡፡

የድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙልነህ ደሳለኝ እንዳሉት ÷ ለትንሳኤ በዓል ከ4 ሺህ በላይ ጤንነቱ የተጠበቀ የእንስሳት እርድ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተጠናቅቋል፡፡

ለእርድ ከተዘጋጁት እንስሳት መካከል 2 ሺህ 600 በሬዎች ሲሆኑ ÷ 1 ሺህ 400 የሚሆኑት ደግሞ በጎችና እና ፍየሎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ለሕብረተሰቡ የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት በቂ የሥርጭት ተሽከርካሪዎችን ከማሟላት ባለፈ ዘመናዊ የእርድ ክፍል ማዘጋጀት መቻሉን ነው ያስረዱት፡፡

ዜጎች ስጋ ለመግዛት ወደ ልኳንዳ ቤቶች ሲያመሩ በአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የታረደ መሆኑንና ስጋው ላይ የማረጋገጫ ማሕተም መኖሩን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የቅድመ እና ድኅረ ዕርድ ምርመራ ከተደረገ በኋላ የዕርድ አገልግሎቱ ኃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ እንደሚከናወን ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

ተሽከርካሪዎች ያለምንም የእንቅስቃሴ ገደብ በፍጥነት ስጋውን ተደራሽ እንዲያደርጉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም አመልክተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ