አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢየሱስ ክርስቶስ በሶስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ የተነሳበት የትንሣኤ በዓል በምስራቅ አውሮፓ ሀገራት በተለያዩ ሀይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡
ከምስራቅ አውሮፓ ሀገራት መካከል ከአጠቃላይ ህዝባቸው 61 በመቶ የሚሆነው የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ ሲሆን በዓለም ካለው አጠቃላይ የእምነቱ ተከታይ 76 በመቶው በዚሁ አካባቢ የሚገኝ ነው፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በዚህ አካባቢ ኢየሱስ በሶስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ የተነሳበትን መለኮታዊ ሁነት በማሰብ በዛሬው ዕለት በተለያዩ አምልኮዎች እና ሀይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡
በምስራቅ አውሮፓ ከኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ጀምሮ የተለያዩ ሀይማኖታዊ ሥርዓቶች የሚከናወኑ ሲሆን መንፈስ ቅዱስን ለመሞላት የእምነቱ ተከታዮች እንደ እንቁላል እና ዳቦ የመሳሉ ነገሮችን በቅርጫት በመያዝ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳሉ፡፡
ዳቦው ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ መመገቡን ለማስታወስ ሲሆን፤ እሁድ ጠዋት ላይ ዳቦውን ሲመገቡ በቅርጫት ቤተ ክርስቲያን ወስደው ፀሎት ያደረጉበትን እንቁላል ደግሞ በመስበር በእንቁላሉ ፈሳሽ ፊታቸውን ይታጠባሉ፡፡
በትንሣኤ ዕለት በቀይ እንቁላል ፊትን መታጠብ ጥንካሬ እና ብርታት የሚሰጥ ሲሆን በነጭ እንቁላል ፊትን መታጠብ ደግሞ ከሀጢያት የመንፃት አምልኮ ነው፡፡
በተመሳሳይ ሳንቲሞችን በመያዝ ፀሎት የሚያደርጉ ሲሆን ይህም የእምነቱ ተከታዮች ፈጣሪ እድገት እና ብልፅግና እንዲያመጣለችው የሚለምኑበት ነው፡፡
ደግሞ መወለድን እና ሞትን ድል መንሳትን በማሰብ በሚከበረው የትንሣኤ በዓል የእምነቱ ተከታዮች አዳዲስ ልብሶች የሚለብሱ ሲሆን፤ ይህም በአካል እና በመንፈስ የመታደስ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ሩሲያ፣ ዩክሬን፣ ፖላንድ፣ ሮማኒያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ሀንጋሪ፣ ስሎቫኪያ፣ ቡልጋሪያ፣ ሞልዶቫ እና ቤላሩስ የትንሣኤ በዓል በድምቀት እየተከበረባቸው የሚገኙ የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት ናቸው፡፡
በሚኪያስ አየለ