አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን ወደቦች ከዛሬ ጀምሮ እንደሚዘጉ ይፋ አድርገዋል፡፡
አሜሪካና ኢራን የመካከኛው ምስራቅ ጦርነትን ለማስቆም ከ47 ዓመታት በኋላ በፓኪስታን ያካሄዱት የፊት ለፊት የሰላም ውይይት ያለስምምነት መጠናቀቁ ይታወቃል፡፡
ይህን ተከትሎም ፕሬዚዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ የሚወሰደው ሁለንተናዊ ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
ከዛሬ ጀምሮም በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚከናወንን የመርከብ እንቅስቃሴ እንደሚያግዱ ገልጸው ÷ ለዚህም የሜሪካ ጦር ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
የፕሬዚዳንቱን ማስጠናቀቂያ ተከትሎም የዓለም የነዳጅ ዋጋ በድጋሚ በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ ማሻቀቡን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሞሃመድ ባጋር ጋሊቢፍ በበኩላቸው ÷ቴህራን አሜሪካ በየጊዜው በምታስተላልፈው የትኛውም ዘቻ እና ማስፈራሪያ እጅ አትሰጥም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የኢራን አብዮታዊ ዘብ ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ የሚጠጉ የጦር መርከቦች ላይ አስፈላጊውን ርምጃ ለመውሰድ በተጠንቀቅ ላይ ይገኛልም ነው ያሉት፡፡
ሀገራቱ በዓለም ቁልፍ የነዳጅ መተላለፊያ መስመር በሆነው ሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የገቡበት እሰጣገባም በዓለም የተፈጠረውን የነዳጅ ቀውስ ይበልጥ እንዳያባብሰው ተሰግቷል፡፡
በመላኩ ገድፍ