የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ እና ላይቤሪያ ወታደራዊ የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ ትብብራቸውን ለማሳደግ ተስማሙ

By Adimasu Aragawu

April 14, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ላይቤሪያ ወታደራዊ የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ ትብብራቸውን ለማሳደግ ተስማምተዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) ከላይቤሪያ ሪፐብሊክ መከላከያ ሚኒስትር ብርጋዲየር ጄኔራል ጄራልዲን ጃኔት ጆርጅ ጋር በአዲስ አበባ ተወያይተዋል።

በዚሁ ወቅት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ወታደራዊ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር በሚቻልባቸው ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) ኢትዮጵያ እና ላይቤሪያ የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት መሆናቸውን አስታውሰው÷ ይህ የታሪክ ትስስር አሁን ላለው ወታደራዊ ትብብር ጠንካራ መሠረት የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በወታደራዊ ኢንዱስትሪና በአቅም ግንባታ ዙሪያ በትብብር ለመሥራት ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

ብርጋዲየር ጄኔራል ጄራልዲን ጃኔት ጆርጅ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ስምሪትን ጨምሮ በወታደራዊ ሳይንስ እና በዘመናዊ መከላከያ ግንባታ ያካበተችው ተሞክሮ ለላይቤሪያ ትልቅ ትምህርት የሚገኝበት መሆኑን ገልጸዋል።

ላይቤሪያ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሰፊ ልምድ የመቅሰም ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላትም አስታውቀዋል።

በተለይም በስልጠና እና በቴክኒክ ዘርፎች የሁለቱን ሀገራት ወታደራዊ ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚሠሩ መናገራቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።