አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ ያላትን ተሞክሮ ለአፍሪካ ሀገራት ለማካፈል ዝግጁ ናት አሉ።
የላይቤሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳራ ቤይሶሎው ኒያቲ የተመራ ልዑክ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን ጎብኝቷል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ተቋሙ የማህበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት በዘርፉ ከጥናትና ምርምር ጀምሮ ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
በገለጻቸውም ኢንስቲትዩቱ በአህጉራዊ ትብብር ላይ በትኩረት እንደሚሰራና ተሞክሮዎቹን ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለማካፈል ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ እያከናወነች ያለውን ተግባር ያደነቁት የላይቤሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ፤ ይህ ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተለይም ለላይቤሪያ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ እየሰራች ያለው ስራ ለአፍሪካ ሀገራት መንገድ አመላካች እና አርአያ መሆኑን ተናግረዋል።
ላይቤሪያ የኢትዮጵያን ተሞክሮ እንደምትወስድ ጠቅሰው፤ ቴክኖሎጂ ለአፍሪካ እድገት ዋስትና እንዲሆን በትምህርት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ጉብኝቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑ ተመላክቷል።