አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከፖርቹጋል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፓውሎ ራንገል ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ጌዲዮን (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷ ኢትዮጵያ እና ፖርቹጋል ረጅም እና ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝም እና አካባቢ ጥበቃ የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
ፓውሎ ራንገል በበኩላቸው÷ በሁለቱ ሀገራት መካከል ቀጥታ የአየር ትራንስፖርት መጀመሩ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ይበልጥ ለማጠናከር መልካም ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አመላክተዋል።
ሁለቱ ሀገራት በቅርቡ የሁለትዮሽ የፖለቲካ ምክክር ለማካሄድ እና በባለብዙ ወገን መድረኮች ላይም በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመላክቷል።