የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ እና ላይቤሪያ ከጋራ የጽናት ታሪክ የሚመነጭ ዘመናትን የተሻገረ ግንኙነት አላቸው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Abiy Getahun

April 14, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ላይቤሪያ ከጋራ የጽናት ታሪክ የሚመነጭ ጥልቅና ዘመናትን የተሻገረ ግንኙነት አላቸው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ኢትዮጵያ የገቡትን የላይቤሪያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ክቡር ጆሴፍ ንዩማ ቦአካይ በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት አቀባበል በማድረጌ ታላቅ ክብር ይሰማኛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና ላይቤሪያ በቅኝ ግዛት ያልተገዙ፣ ለአኅጉሩ ነፃነትና አንድነት ድምፅ በመሆን ከጋራ የጽናት ታሪክ የሚመነጭ ጥልቅና ዘመናትን የተሻገረ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተዋል።

ዛሬም እንደ ሁሌው ኢትዮጵያ ከሰፊ ገበታዋ ያላትን ታላቅ ዐቅምና ዘላቂ ወዳጅነት፣ አብረዋት ለሚጓዙ ሁሉ ለማካፈል ዝግጁ ናት ብለዋል።

በዚህ መንፈስ ይህ ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማጠናከር፤ የጋራ ህልሞቻችንን በማይናወጥ መሠረት እና የመፈጸም ቁርጠኝነት ወሳኝ ምዕራፍ እንደሚሆን ጽኑ እምነት አለኝ ሲሉ ገልጸዋል።