የሀገር ውስጥ ዜና

ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ ልብ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Abiy Getahun

April 14, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ ልብ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የሉዓላዊነት ልብ” በሚል መሪ ሐሳብ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ነው ይህንን የገለጹት።

በቆይታቸው የመደመር መንግሥት ማዕከላዊ ዕሳቤ ስለሁሉ ነገር ሚዛን መጠበቅ እንደሆነ ገልጸው÷ የሆኑ መንግሥታት አብዛኛውን ዕሳቤያቸውን ፖለቲካ ላይ አድርገው ኢኮኖሚን ተከታይ አድርገው ሞክረውታል ነገር ግን ይህ አካሄድ እምብዛም አዋጭ አልነበረም ብለዋል።

ሌሎች ደግሞ አብዛኛውን ነገራቸውን ኢኮኖሚ ላይ አድርገው ሞክረዋል፤ እሱም የራሱ የሆነ ውስንነት አለበት ነው ያሉት።

በፖለቲካና በኢኮኖሚ መካከል ሚዛን መጠበቅ ፖለቲካል ኢኮኖሚን በትክክል መግራትና መረዳት አስፈላጊ ነው በማለት ገልጸው÷ የመደመር መንግሥት በሚዛን የሚነሳ ነው፤ አንዱ ገዝፎ አንደኛው ያነሰ እንደሆነ የሚፈለገውን ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ያስቸግራል ብለዋል።

ትኩረታችን ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ላይ የሆነበት ዋናው ምክንያት ኢንዱስትሪ ለማደግና ለመለወጥ ለሚፈልግ ሀገር ሁሉ በጣም ወሳኝ ነገርና የኢኮኖሚ ልብ በመሆኑ ነው ሲሉም አብራርተዋል።

የኢኮኖሚ ልብ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ አንዳንዶች የኢኮኖሚ ሞተር እንደሚሉም አስረድተዋል።

ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ያለው ሚና ከሌሎች ጋር የሚወዳደር አይደለም ነው ያሉት።

ለወጪ ንግድ ብዛትም ሆነ ጥራት ወሳኝ እንደሆነ አንስተው÷ ይህንንም ውጤታማ ለማድረግ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በፈጠራና ቴክኖሎጂ አንጻር የሚያመጣው ለውጥ ለራሱ ብቻ አለመሆኑን ገልጸው÷ ለሌሎች ዘርፎችም ጭምር እንደሆነ አብራርተዋል።

ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንፃርም በርካታ የስራ ዕድሎችን የሚፈጥርና ኢኮኖሚውን እንደሚያሻግር ጠቅሰው፤ በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነት አንዱ አንጓ ነው ብለዋል።

ከአንድ የኢኮኖሚ ዘውግ ወደ ሌላው የኢኮኖሚ ዘውግ ለመሸጋገር የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አይተኬ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል።

በአድማሱ አራጋው