ቢዝነስ

የኢትዮጵያ ምርቶች በቀጥታ ለሩሲያ ገበያ የሚቀርቡበት የኦንላይን የግብይት መድረክ ይፋ ሆነ

By Adimasu Aragawu

April 15, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩሲያው ግዙፍ ኢ-ኮሜርስ ኩባንያ ዋይልድቤሪስ ኢትዮጵያውያን አምራቾች እና ነጋዴዎች ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለሩሲያ ገበያ የሚያቀርቡበትን የኦንላይን የግብይት መድረክ በይፋ አስጀምሯል።

ኩባንያው በመጀመሪያው ምዕራፍ የቡና፣ የጨርቃጨርቅና የቆዳ ውጤቶች፣ የተፈጥሮ መዋቢያዎች እንዲሁም የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች በገበያ ትስስሩ ይቀርባሉ ብሏል።

የዕቃ ማጓጓዝና የሎጂስቲክስ ስራውን ለማቀላጠፍ ኩባንያው ከኢትዮ ፖስታ ጋር በሽርክና የሚሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ይድነቃቸው ወርቁ፤ የኩባንያው ጅምር የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራተጂን እውን ለማድረግ እና ዲጂታል ንግድን እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የዋይልድቤሪስ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ብሩክ ገነነ በበኩላቸው፤ ተቋሙ የሀገር ውስጥ አምራቾች እንደ ቡና፣ ጨርቃጨርቅ እና የቆዳ የመሳሰሉ ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለዓለም አቀፍ ገበያ እንዲያቀርቡ ሰፊ እድል ይፈጥራል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የዲጂታል ንግድን በማስፋፋት የሀገር ውስጥ ምርቶችን የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ኩባንያው ከ20 ዓመታት በላይ ልምድ ያለው እና ከ81 ሚሊየን በላይ ደንበኞች እንዳለው ጠቅሰው፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጋር በፈጠረው ስምምነት መሰረት በኢትዮጵያ የዲጂታል ንግድ መሠረተ-ልማት ለማዘመን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት የሀገር ውስጥ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ላይ ያተኮረው ኩባንያው በቀጣይ አሰራሩን በማስፋት የተለያዩ ምርቶችን ለኢትዮጵያውያን ተጠቃሚዎች ለማቅረብ አቅዷል።

በሳራ ስዩም