አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለዋናው ሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የመለየት ስራው እየተጠናቀቀ ይገኛል አሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም።
ኮሚሽነር መላኩ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ለዋናው ጉባኤ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው÷ ኮሚሽኑ ባለፉት ጊዜያት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን አጀንዳ ማሰባሰቡንና ተወካዮች ማስመረጡን ተናግረዋል።
አሁን ላይ አጀንዳ የመለየት ስራው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝና የተለዩ አጀንዳዎችን ለባለድርሻ አካላት በማቅረብ ሐሳብ መሰብሰብ፣ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤውን አጀንዳዎች መቅረጽ እና አመካካሪዎችን በስልጠና ዝግጁ ማድረግ ቀጣይ ስራዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።
ሀገራዊ የምክክር ጉባኤውን መጥራት፣ መመካር፣ መግባባት ላይ የተደረሰባቸውን ጉዳዮች ማጠናቀር እና ለሚመለከታቸው አካላት ማቅረብ፣ ተግባራዊነታቸውን መከታተል እና ለሕዝቡ ይፋ ማድረግ እንደሚገኝበትም ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ የተካሄደው የትግራይ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ እና ተወካዮችን የማስመረጥ የምክክር ምዕራፍ ከዕቅዳችን በላይ የተከናወነ ነው ብለዋል።
ከተሰበሰበው አጀንዳ እና ከተሳታፊ ስብጥር አንጻርም አመርቂ ሊባል የሚችል እንደሆነ አመልክተዋል።
በመሳፍንት እያዩ