በደብረ ብርሃን ከተማ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች የተለያየ የምግብ አይነት ድጋፍ ተደርጓል፡፡
ድጋፉን የኢትዮጵያ አዲስ ኪዳን መጥምቃዊት ቤተ ክርስቲያን ልማት ኮሚሽን ከኮምፓሽን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ነው ያደረጉት፡፡
በድጋፍ ማስረከቢያ መርሐ ግብሩ ላይ የልማት ኮሚሽኑ ኤክስኪውቲቭ ዳይሬክተር አቶ ማሞ ቀጸላ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ፕሬዚዳንት መጋቢ ታዬ ደገፋ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቦርድ ሰብሳቢ (ዶ/ር ኢ/ር) ብዙአየሁ አበበ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
የተደረገው ድጋፍ 334 ኩንታል ጤፍ፣ 34 ኩንታል ባቄላ፣ ከ100 ኩንታል በላይ አልሚ ምግብና 1 ሺህ 115 ሊትር ዘይት ያካተተ መሆኑን አቶ ማሞ ቀጸላ ተናግረዋል፡፡
በዚህም 2 ሺህ 227 ተፈናቃዮች ተጠቃሚ መሆቸውን ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡
የልማት ኮሚሽኑ ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
ዜጎች ቸግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሚችሉትን ድጋፍ በማድረግ አብሮነታቸውን ማሳየት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡