አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ባለፉት 9 ወራት ለ2 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል ተፈጥሯል አሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ መስፍን መላኩ።
ከመደመር መንግሥት እሳቤ በተቀዳ ስትራቴጂ በክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ክህሎት ያለው ወጣት ለማፍራት፣ ኢንተርፕርነሮችን ለማብዛት እና አግልግሎትን ለማዘመን በተከናወኑ ተግባራት ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
በዚህም ባለፉት 9 ወራት ለ2 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸው፤ የስራ ዕድሎቹ 28 ቢሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ፣ 95 ሺህ ሄክታር መሬት እና 5 ሺህ የማሽነሪ የድጋፍ ጥቅሎች የተፈጠሩ ናቸው ነው ያሉት።
በከተማ ግብርና ኢኒሼቲቭ በተገነቡ 139 ሺህ ሼዶች ከ61 ሚሊየን በላይ እንስሳቶች እንደሚገኙና ማዕከላቱ ከፈጠሯቸው የስራ ዕድሎች ባሻገር የኑሮ ጫና ያቀለሉና የገጠር ሽግግርን ያፋጠኑ መሆኑን አብራርተዋል።
ከተቋቋሙ 18 ሺህ ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች መካከል ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑት መሰረተ ልማት እንዲሁም ማሽነሪዎች ተሟልቶላቸው ወደ ስራ መግባታቸውንና በእነዚህ ኢኒሼቲቮች ብቻ ለ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን አንስተዋል።
ከለውጡ በፊት በክልሉ ከ10 ሺህ የማይበልጡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ብቻ እንደነበሩ በማስታወስ አሁን ላይ 40 ሺህ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መኖራቸውን አመልክተዋል።
ከነዚህም ውስጥ ከ11 ሺህ በላይ የሚሆኑት በክልሉ ኢንቨስትመንት ቦርድ ባለፉት 9 ወራት ውሳኔ የተላለፈባቸው እንደሆኑ ተናግረዋል።
በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ለመቅረፍ 17 መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቁመዋል።
ባለፉት 9 ወራት በኮሪደር ልማት ስራ 115 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ፣ 90 ኪሎ ሜትር የሳይክል መንገድ፣ 817 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ፣ 90 የመኪና ማቆሚያዎችና 40 የልጆች መጫወቻና የስፖርት ማዕከላት መገንባታቸውንም ጠቅሰዋል።
በመራኦል ከድር