አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመሩ ስራዎችን በከፍተኛ ክትትል በማጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሰረት መጣላችንን እንቀጥላለን አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ለኢትዮጵያ አምስተኛ የሆነውን በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን በመረቁበት ወቅት ነው።
በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በዘርፉ በሰራነው ሪፎርም ባለፉት ዓመታት 4 ሺህ የነበረው ሜጋ ዋት ወደ 10 ሺህ ሜጋ ዋት ማደግ ችሏል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ወደ አትራፊነት መሸጋገር መቻሉን ጠቅሰው፤ ባለፉት ስድስት ወራት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 7 ቢሊየን ብር ትርፍ ማስገባቱን ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ መጀመር ብቻ ሳይሆን መጨረስ፣ መክሰር ብቻ ሳይሆን ማትረፍ የተለማመድንበት ስራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ 145 ሚሊየን ዩሮ ገደማ ወጪ እንደወጣለት ተናግረዋል።
ከሁለት አመት በኋላ ፕሮጀክቱ ይህንን ገንዘብ መመለስ እንደሚችል ጠቅሰው፤ ይህም ልጆቻችን ትርፍ እንጂ እዳ የሚረከቡ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል ብለዋል።
የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል ኢንዱስትሪ፣ መንገድ፣ ግብርና፣ የሶላር ኢነርጂ በአጠቃላይ ሁሉንም ዘርፍ በማዘመንና በማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች በከፍተኛ ክትትል በማጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሰረት መጣላችንን እንቀጥላለን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ በየትኛውም አይነት አጀንዳ አይደናቀፍም በማለት ገልጸው፤ የምናደርገው የህዝብን ህይወት መለወጥ ነው ሲሉም አንስተዋል።
በርከት ያሉ ስራዎች እንደተጀመሩና ወደ መጠናቀቅ መቅረባቸውን በመግለጽ፤ ስራዎች በሙሉ አቅም እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
በሶስና አለማየሁ