አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የአፍሪካ ሕብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስትራቴጂ ግንባታን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል አሉ።
በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ አስተዳደር እና ጸጥታ ዙሪያ ላይ ያተኮረ የአፍሪካ ህብረት ሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት የሚኒስትሮች ስብሰባ በበይነ መረብ ተካሄዷል።
የወሩ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት ሊቀመንበሯ ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) መድረኩን መርተውታል።
በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሕብረቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ ሰላም እና ጸጥታ አማካሪ ቡድን ማቋቋም ተገቢ ነው ብለዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ የአስተዳደር፣ የኢኮኖሚ ልማት እና ደኀንነት ጉዳዮች በፍጥነት እየለወጠ እንደሚገኝና በአፍሪካም መልካም ዕድሎችን እና ስጋቶችን ጭምር ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል።
በዚህም ግጭትን ቀድሞ ለመከላከል፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያዎችን ለመተግበር፣ የሽምግልና ጥረቶችን ለመደገፍ እና አጠቃላይ በአሕጉሪቱ የአስተዳደር ሥርዓቶችን በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለው አብራርተዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት ከአግባብ ውጭ ጥቅም ከዋለ የሳይበር ወንጀሎች እንዲበራከቱ፣ ለሽብርተኛ ድርጅቶች እና ተባባሪዎቻቸው ጥቅም ሊውል ስለሚችል አስፈላጊውን ማዕቀፍ ማውጣት እና ማጠናከር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
መንግሥታትና ተቋማት በውሳኔ አሰጣጥ ሒደት፣ በሕዝብ አስተዳደር፣ በደኀንነት ሥርዓት እና በኢኮኖሚ ዕቅዳቸው ጋር ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በተቀናጀ መንገድ የመጠቀም ልምዳቸው እየጨመረ መምጣቱን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና በዲጂታል ጤና የአፍሪካ ህብረት ሻምፒዮን ተደርገው መሰየማቸውን አስታውሰው፤ ይህም ዲጂታል አጀንዳን የበለጠ ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ እንደሆነ አመልክተዋል።
በሕብረቱ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሒሩት ዘመነ፥ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ስትራቴጂን በተግባር መተርጎም እንደሚገባና ማስገንዘባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።