አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ባለፉት 9 ወራት 21 ሺህ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአግልግሎት ዝግጁ ሆነዋል አሉ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዲ።
በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመት ከተጀመሩ ከ28 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች መካከል 21 ሺህ የሚሆኑት መጠናቀቃቸውን ገልጸው÷ የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በከፍተኛ ጥራትና ፍጥነት የተከናወኑ መሆናቸውን አመላክተዋል።
ፕሮጀክቶቹ 97 ከመቶ በማሕበረሰብና በመንግስት ተሳትፎ የተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ ቀሪው 3 በመቶ ደግሞ በተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ የልማት ድርጅቶች የተከናወኑ ናቸው ብለዋል።
የክልሉ መንግስት ዕቅዶቹን በመፈጸም የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ 400 ቢሊየን ብር በጀት ይዞ ወደ ተግባር መግባቱንም ነው የገለጹት።
በጀቱን ከብክነት በፀዳ መልኩ በመጠቀም ባለፉት 9 ወራት 81 በመቶ ያህሉ ለመሰረታዊ የልማት መስኮች መዋሉን አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል በክልሉ ያሉ አቅሞችን በመለየትና የግብር ከፋይ ዜጎችን ግንዛቤ በማሳደግ ባለፉት 9 ወራት ከ237 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በዚህም የክልሉን ወጪ 80 በመቶ በራስ አቅም መሸፈን ተችሏል ብለዋል።
በክልሉ ያሉ የልማት እድሎችን በአግባቡ መጠቀም እና የክልሉን ገቢ ማሳደግ መቻሉ ለታየው ፈጣን እድገት አስተዋጽዖ ማድረጉንም ተናግረዋል።
በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ለመቅረፍ ወደ ስራ በገቡ 26 መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተቋማት ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች አገልግሎት ማግኘታቸውንም አመላክተዋል።
በዚህም በክልሉ የነበረው የተገልጋይ እርካታ መጠን ከነበረበት 54 በመቶ ወደ 97 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጸው÷ ከምርጫ በፊት መሶብ የአንድ ማዕከልን በክልሉ 91 ከተሞች ወደ ስራ ለማስገባት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አገልግሎትን በዜጎች ደጃፍ ለማድረስ በተተገበረው የአስተዳደር ስርዓት ከወረዳ ወደ 7 ሺህ ቀበሌዎች የማውረድ ተግባር ሰፊ ውጤት የተገኘበት መሆኑን ጠቅሰው÷ 50 ሺህ ሕዝባዊ ወገንተኝነት ያላቸውና የሰለጠኑ ወጣቶች የተለያዩ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋልም ነው ያሉት።
በክልሉ በተለያዩ መዋቅሮች በብልሹ አሰራሮች ላይ በተሳተፉ ከ10 ሺህ በላይ አመራሮች ላይም አስተዳደራዊ ርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።
በመራኦል ከድር