የሀገር ውስጥ ዜና

አፋርን የዓለም የሳይንስና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ …

By Melaku Gedif

April 17, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰው ልጅ የታሪክ መጽሐፍ የመጀመሪያው ምዕራፍ የሆነው የአፋር ክልል በተለይም የአዋሽ ተፋሰስ እንደ ሉሲ (ድንቅነሽ)፣ አርዲ እና ሰላም ያሉ የሰው ልጅ ቅድመ አያቶች ቅሪተ አካላት የተገኙበት ነው፡፡

ክልሉ በዓለም የሳይንስ ሊቃውንት ዘንድ የሰው ዘር መገኛ የሚል ታላቅ ስም የተሰጠው ሲሆን÷ ይሁን እንጂ ይህ የዓለም ሁሉ ኃብት የተገኘበት አካባቢ ግኝቶችን በዝርዝር የሚያሳይና ታሪካቸውን በአግባቡ የሚተርክ ዘመናዊ ሙዚዬም በአካባቢው አልነበረም።

አሁን ላይ ታዲያ ይህንን ዓለም አቀፍ ሃብት ለማሳየት የሚያስችል ሙዚዬም በአፋር ክልል የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን በ329 ሚሊየን ብር ወጪ ለመገንባት ወደ ሥራ ገብቷል።

ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎችን የያዘው ይህ ሙዚዬም ለምርምርና ለሳይንሳዊ እድገት፣ ለማህበራዊና አካባቢያዊ ልማት፣ ለቱሪዝም እድገት እና ለሀገር ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አበርክቶ ይኖረዋል።

በምርምርና በሳይንሳዊ ዕድገት ረገድ ሙዚዬሙ መገንባቱ ለሀገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች ትልቅ የምርምር ማዕከል ሆኖ የሚያገልግል ሲሆን ÷ ተመራማሪዎች ቅሪተ አካላቱ በተገኙበት አካባቢ ሆነው ጥናት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።

ከዚህ ባለፈም የኢትዮጵያ ተመራማሪዎች ከዓለም አቀፍ ሳይንቲስቶች ጋር በቀጥታ እንዲገናኙና ልምድ እንዲቀስሙ መንገድ የሚከፍት ሙዚዬም ነው።

ከማህበራዊና አካባቢያዊ ጥቅሞች አንጻር ለአፋር ማሕበረሰብ የማንነት ኩራት የሆነ፤ ሃብቱን በባለቤትነት ስሜት እንዲጠብቅና በታሪኩ እንዲኮራ ከማድረግ ባሻገር ለአካባቢው ተማሪዎችና ወጣቶች ስለ ሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥና ታሪክ በተግባር የታገዘ ትምህርት እንዲያገኙ ያስችላል።

ሙዚዬሙ በክልሉ ያለውን የቱሪዝም ፍሰት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ረገድም የቱሪዝም ሞተር በመሆን ቱሪስቶች ቅሪተ አካላቱ የተገኙበትን ቦታ ብቻ ሳይሆን በሙዚዬሙ የተደራጁ መረጃዎችን ለማግኘት ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ እንዲሁም ለሆቴሎች፣ ለትራንስፖርትና ለሀገር በቀል የእጅ ጥበብ ውጤቶች ገበያ ይፈጥራል።

በሌላ በኩል የሰው ዘር መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ይበልጥ ለማስተዋወቅ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ መሳሪያ የመሆን አቅም አለው፡፡

ቅሪቶች በሳይንሳዊ መንገድ ተጠብቀው የሚቀመጡበት ማዕከል መኖሩ ሀገሪቱ ለቅርስ ጥበቃ የምትሰጠውን ትኩረት በማሳየት የሀገር ገጽታን የሚገነባ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡

የሰው ልጅ ሁሉ መነሻ የሆነውን ምድር፣ የሰው ልጆችን አንድነት እና የኢትዮጵያን ጥንታዊነት አጉልቶ የሚያሳየው ሙዚዬሙ የሰላም ተምሳሌት ከመሆን ባሻገር አፋርን የዓለም የሳይንስና የቱሪዝም ማዕከል በማድረግ ታሪክን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ ያስችላል፡፡