አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባዔ (ኮፕ32) ለማስተናገድ ዝግጅቷን ቀደም ብላ ጀምራለች አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ የኮፕ32 አስተናጋጅ እንደሆነ ሀገር፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ኮሚቴ በይፋ በማቋቋም ዝግጅቷን ቀደም ብላ ጀምራለች ብለዋል።
ይህን ሒደት በግልጽ ግብ እና በላቀ ምልከታ ለመምራት ቁልፍ አመራር መመደቡን ገልጸው÷ ይህን ተከትሎ የኮፕ ፕሬዚዳንት መዋቅር የተቀናጀና የላቀ ውጤት የሚያስገኙ የቅድሚያ ተግባራቱን እንደጀመረ አመልክተዋል፡፡
በዛሬው ዕለት ከብሔራዊ ኮሚቴው ጋር በነበራቸው ስብሰባ በተለያዩ ዘርፎች የተከናወኑ የእስካሁን ሥራዎች መገምገማቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ክፍተቶችን የመለየት እና ሁሉም ጥረቶች ከሀገራዊ ርዕይ ጋር የተጣጣሙ መሆናቸው እንደተዳሰሰ ጠቁመዋል።
በመድረኩ ከግምገማ ባሻገር የጋራ ቀጣይ አቅጣጫ እንደተቀመጠም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስገነዘቡት።
በጠንካራ ትብብር፣ በተዋሃደ ታላቅ ርዕይ እና የጋራ ጽኑ ትጋት በመናበብ ይህን ዓለም አቀፍ ሁነት በልህቀት በማስተናገድ የሀገርን ታላቅነት ዳግም ማሳየት ግልጽ ትኩረታችን ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።