የሀገር ውስጥ ዜና

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአፈር ማዳበሪያን ለአርሶ አደሮች በወቅቱ ለማሰራጨት እየተሰራ ነው

By Melaku Gedif

April 17, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለመኸር እርሻ የአፈር ማዳበሪያን በወቅቱ ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ፡፡

በቢሮው የግብዓት አቅርቦት ዳይሬክተር ተስፋዬ በቀለ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ለምርት ዘመኑ የሚያስፈልጉ የግብርና ግብዓቶችን በተገቢ ሁኔታ ለአርሶ አደሮች ማሰራጨት ይገባል፡፡

በክልሉ በግብርና ግብዓት ሥርጭት ሒደት ላይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ ሥራ መጀመሩን አመልክተዋል፡፡

ለመኸር እርሻ 131 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት መታቀዱን ጠቁመው÷ ከዚህ ውስጥ 98 ሺህ ኩንታል ወደ ክልሉ መግባቱን ጠቅሰዋል፡፡

እስካሁን በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ መሰራጨቱን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡

በሌላ በኩል ለምርት ዘመኑ ከ9 ሺህ 400 ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለማሰራጨት ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር በበቂ ሁኔታ ለአርሶ አደሮች እንዲደርስ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ