ስፓርት

ቼልሲ ከማንቼስተር ዩናይትድ …

By Abiy Getahun

April 18, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ33ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ቼልሲ ከማንቼስተር ዩናይትድ የሚያደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡

ሁለቱም ቡድኖች የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ ቦታን ለማግኘት የሚያደርጉትን ጉዞ አጠናክረው ለመቀጠል የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል፡፡

በሊጉ ያለፉትን ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች የተሸነፈው ቼልሲ ወደ ድል ለመመለስ ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል፡፡

በአሰልጣኝ ሊያም ሮሲኒየር ቅጣት ተላልፎበት ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ለቼልሲ ግልጋሎት ያልሰጠው ኢንዞ ፈርናንዴዝ በምሽቱ ጨዋታ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ አሰልጣኙ አረጋግጠዋል፡፡

በሊጉ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ድል ያላደረገው ተጋጣሚው ማንቼስተር ዩናይትድ ወደ ድል ለመምጣት የሚያደርገው ፉክክር ተጠባቂ ነው፡፡

ማንቼስተር ዩናይትድ በሊድስ ዩናይትድ በተሸነፈበት ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው የተከላካይ ሥፍራ ተጫዋቹ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ በምሽቱ ጨዋታ ለቀያይ ሰይጣኖቹ ግልጋሎት አይሰጥም፡፡

ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፉ በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል፡፡

በዚህ የውድድር ዓመት በኦልድትራፎርድ ያደረጉትን የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ማንቼስተር ዩናይትድ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

ተጠባቂው ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም መደረግ ይጀምራል፡፡

በሌላ የሊጉ ጨዋታ ምሽት 1 ሰዓት 30 ላይ ቶተንሃም ሆትስፐር በሜዳው ብራይተንን ያስተናግዳል፡፡

በ30 ነጥብ ወራጅ ቀጣና 18ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶተንሃም ሆትስፐር በሊጉ ከወራጅ ቀጣናው ለመውጣት የሚደያርገው ብርቱ ፉክክር ይጠበቃል፡፡

በሊጉ ከ19ኛ ሳምንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ድል ማድረግ የተሳነው ቶተንሃም ሆትስፐር ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡

ያለፉትን ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ያደረገው ተጋጣሚው ብራይተን በበኩሉ አሸናፊነቱን ለማስቀጠል ይፋለማል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ብራይተን ሦስቱን ሲያሸንፍ ቶተንሃም ሆትስፐር በአንዱ ድል አድርጎ በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል፡፡

ከእነዚህ ጨዋታዎች አስቀድሞ ቀን 8 ሰዓት 30 ላይ ብሬንትፎርድ ከፉልሃም ሲገናኙ ሊድስ ዩናይትድ ከወልቭስ እንዲሁም ኒውካስል ዩናይትድ ከቦርንማውዝ በተመሳሳይ አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ የሚደረጉ ሌሎች የሊጉ ጨዋታዎች ናቸው፡፡

ሊጉን አርሰናል በ70 ነጥብ ሲመራው ማንቼስተር ሲቲ በ64 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

ማንቼስተር ዩናይትድ በ55 ነጥብ 3ኛ እንዲሁም አስቶንቪላ በተመሳሳይ 55 ነጥብ በግብ ክፍያ አንሶ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ወራጅ ቀጣናው ላይ ቶተንሃም ሆትስፐር፣ በርንሌይ እና ወልቭስ እንደ ቅድም ተከተላቸው ከ18ኛ እስከ 20ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡

የሊጉን ኮከብ ግብ አስቆጣሪነት ኤርሊንግ ብራውት ሃላንድ በ22 ግቦች ሲመራ÷ ኢጎር ቲያጎ በ21፣ አንቷን ሴሜኒዮ በ15 እንዲሁም ጇ ፔድሮ በ14 ግቦች ይከተላሉ፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ