የሀገር ውስጥ ዜና

ኮፕ32 ዘላቂ ትሩፋት ያለው ሆኖ እንዲያልፍ ለማድረግ ይሰራል – ዓለምጸሐይ ጳውሎስ

By Adimasu Aragawu

April 18, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 32ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ32) ሂደት ዘላቂ የሆነ ትሩፋት ያለው ሆኖ እንዲያልፍ ለማድረግ ይሰራል አሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምጸሐይ ጳውሎስ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ32ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ32) ብሔራዊ ኮሚቴ የተከናወኑ ሥራዎችን ገምግመዋል፡፡

ዓለምጸሐይ ጳውሎስ በዚሁ ወቅት÷ የኮፕ32 መሠረተ ልማት፣ ሎጂስቲክስ እና ኦፕሬሽን ግብረ ኃይል የተከናወኑ ተግባራትን እና ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮችን በሚመለከት ለኮፕ32 ‎ብሔራዊ ኮሚቴ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም የግብረ ኃይሉ ዓላማ ጉባዔው ከመካሄዱ በፊት አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን በማሟላት፤ ጉባዔው በሚካሄድበት ወቅት የተሳለጠ እንዲሆን እንዲሁም ጉባኤው ከተጠናቀቀ በኋላ ትውልድ ተሻጋሪ የሆነ ዕሴት አሳርፎ ማለፍ እንዲችል ማድረግ ነው ብለዋል።

በዚህም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እና መስፈርቶችን የሚያሟሉ መሠረተ ልማቶች የሚገነቡ እንዲሁም ከተለያዩ አካላት የሚሰባሰቡ አስፈላጊ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ የተሳለጠ እና ስኬታማ ጉባዔ ከማካሄድ በተጨማሪ ወደ ትውልድ መሻገር የሚችሉ፣ ዘላቂ እና ለቀጣይ ስራዎቻችን አጋዥ የሚሆኑ መሠረተ ልማቶች መገንባትን ታሳቢ ያደረገ ዓላማን በመያዝ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ግብረ ኃይሉ መሠረታዊ የሚባሉ ግቦችን በመለየት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸው÷ የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የሚያሟሉ እና ጉባዔውን የሚያሳልጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ የመጀመሪያው ግብ መሆኑን አመላክተዋል።

የተገነቡ መሠረተ ልማቶች እንግዶች በጉባዔው ለመሳተፍ ሲመጡ ከአቀባበል ጀምሮ እስከሚሸኙበት ጊዜ ድረስ ደረጃውን የሚመጥን እንቅስቃሴዎች እንዲኖሩ በማድረግ ስኬታማ ጉባዔ እንዲካሄድ መሠረታዊ ጉዳዮችን የያዘ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ሂደት ነባሩ የከተማ እንቅስቃሴ እና የሕብረተሰብ አገልግሎት እንደተጠበቀ ሆኖ ነባሩን ሳይረብሽ አዲስ የሚመጣውን መቋቋም የሚችል የማይበገሩ መሠረተ ልማቶች መኖራቸውን የማረጋገጥ ግብ ሌላኛው ትኩረት የተደረገበት እንደሆነ ገልጸዋል።

በሂደቱ የሚፈጠሩ አቅሞች በተለይም ወጣቶች በሂደት ውስጥ እንዲያልፉ በማድረግ የሀገር ውስጥ አቅምን መገንባት የሚያስችል ስራ እንደሚሰራም አብራርተዋል።

በተጨማሪም ሙሉ ሂደቱ ዘላቂ የሆነ ትሩፋት ያለው ሆኖ እንዲያልፍ ማድረግን ታሳቢ በማድረግ እንደሚሰራ ገልጸው÷ ጉባዔው ከተለያዩ ጉዳዮች አኳያ ደኅንነቱ የተጠበቀ ሆኖ እንዲካሄድ የሚያስችል ግቦችን በመያዝ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዮናስ ጌትነት