ፋና ስብስብ

ከአፍሪካ ኢትዮጵያን ምርጫ ያደረገው እውቁ ብሎገር…

By Adimasu Aragawu

April 18, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተለያዩ የማሕበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነው ሀሪ ጃጋርድ ከአፍሪካ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን ምርጫው አድርጓል።

እንግሊዛዊው ብሎገር ሀሪ ጃጋርድ በፌስቡክ 5 ሚሊየን እንዲሁም በዩቲዩብ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ተከታዮች ያሉትት ሲሆን÷ 7 አሕጉራት፤ 7 ሀገራት ወይም “7 Continents, 7 Countries, No Excuses” በሚል ዓለም አቀፋዊ ጉዞው ነው ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ብቸኛ መዳረሻ አድርጎ የመረጣት።

ሀሪ ጃጋርድ ኢትዮጵያን እንዲመርጥ ያደረገው ደግሞ ያላት ጥንታዊ ታሪክ፣ አስደናቂ የተፈጥሮ ውበት እና ልዩ እንግዳ ተቀባይነት መሆኑ ተገልጿል።

ይህም ለኢትዮጵያ በዓለም መድረክ በድጋሚ ምስክርነት የተሰጠበት ሆኗል።

ብሎገሩ በጉዞው “ምንም ሰበብ የለም” በማለትም ኢትዮጵያ ለማንኛውም ዓለም አቀፍ ተጓዥ ቀዳሚ መዳረሻ መሆን እንደምትችል አሳይቷል።

ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እያከናወነች በምትገኘው ስራ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው ሰዎች ዓይን ማረፊያ እየሆነች ትገኛለች።

ይህም ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ፣ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት እና የመስተንግዶ ጥግ መሆኗን ለዓለም የምናሳይበት ሌላው አጋጣሚ እየሆነላት ነው።

ከዚህ በፊትም በዩቲዩብ ከፍተኛ ተከታይ ያለው አይሾው ስፒድ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የኢትዮጵያን ውበት በሚሊየን ለሚቆጠሩ የዓለም ሕዝቦች በቀጥታ ሥርጭት ማሳየቱ አይዘነጋም።