አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ለኢትዮጵያ የማደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሬ እቀጥላለሁ አለ፡፡
በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ የተመራ ልዑካን ቡድን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ጋር ተወያይቷል፡፡
የኢትዮጵያ ልዑካን በዚህ ወቅት÷ በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተከናወኑ ሥራዎችንና የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን ጨምሮ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የልማት ቅድሚያዎችን ለማሳደግ ወቅታዊ ሊተነበይ የሚችልና የተስፋፋ ዓለም አቀፍ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ በበኩላቸው ÷በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ሪፎርም አጀንዳ ላይ ቀጣይነት ያለው መሻሻል እንደታየ መናገራቸውን ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
በዚህም ከዓለም ባንክ ጋር በቅርበት በመተባበር ጠንካራና የተቀናጀ ድጋፍ ለመስጠት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።