የሀገር ውስጥ ዜና

የሀሮ ደንዲ ሎጅ ዘመናዊ ሥነ ሕንጻ ከተፈጥሮ ጋር የተዋሃደበት የኢትዮጵያ አዲስ ገጽታ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Abiy Getahun

April 19, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሀሮ ደንዲ ሎጅ ዘመናዊ ሥነ ሕንጻ ከተፈጥሮ የልብ ትርታ ጋር የተዋሃደበት የኢትዮጵያ አዲስ ገጽታ ነው አሉ፡፡

በኦሮሚያ ክልል የገበታ ለትውልድ መርሐ ግብር አካል የሆነው የሀሮ ደንዲ ሎጅ ‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተመርቋል፡፡

‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ይህ ስፍራ የተፈጥሮን ሥነ ምህዳር የጠበቀ የቱሪዝም መዳረሻ ከመሆኑ ባለፈ፣ ዘመናዊ ሥነ ሕንጻ ከተፈጥሮ የልብ ትርታ ጋር የተዋሃደበት የኢትዮጵያ አዲስ ገጽታ ነው ብለዋል።

በዚህ ቦታ የቆመው ግንባታ ብቻ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይልቁንም የተፈጥሮ ቅርሳችንን በማክበር የደንዲ ክሬተር ሐይቅን ነባራዊ ውበት ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተርፍ መደረጉን አመልክተዋል፡፡

ይህም የአካባቢውን ማህበረሰብ ባህላዊ እሴት ባከበረ እና ሰው ተኮር በሆነ መልኩ መሬቱን ለመንከባከብና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተገነባ ስፍራ ነው ብለዋል።

‎የሀሮ ደንዲ ሎጅ የገባነውን ቃል ፈጽመን የመገኘታችን ተጨማሪ ማረጋገጫ ነው ሲሉም አስረድተዋል።

ሎጁ እና የአካባቢው አስደናቂ ሥነ ምህዳር ኢትዮጵያን ለመጎብኘት፣ ለኢንቨስትመንት እና ለሁነት ቱሪዝም ተመራጭ መዳረሻ እንደሚያደርጋት አብራርተዋል፡፡

‎ቱሪዝም የኢኮኖሚያችን አንዱ ምሰሶ እንደመሆኑ፣ የሀገራዊ ዕድገታችንን የወደፊት አቅጣጫ እየቀረጸ ያለ ዘርፍ መሆኑን እያስመሰከረ ነው ብለዋል፡፡