አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የምትሰራው በአባቶቻችን ደም ብቻ ሳይሆን በእኛም ላብ እንደሆነ አምነን እየሰራን ነው አሉ፡፡
በኦሮሚያ ክልል የገበታ ለትውልድ መርሐ ግብር አካል የሆነው የሀሮ ደንዲ ሎጅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተመርቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ብዙ ሰዎች የእኛን ስራ በቱሪዝም ለመለካት መሞከራቸው የተሳሳተ በመሆኑ ፖሊሲዎቻችን እና ስትራቴጂዎቻችንን በደንብ ማየት ጠቃሚ ነው ብለዋል።
የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) የዚህን ዓመት ሀገራትን የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ ሲያስቀምጥ ከአፍሪካ ውስጥ ቁጥር አንድ ዕድገት ያላት ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗን መግለጹን ጠቅሰዋል።
ዕድገቱ በምን መጣ ቢባል በቱሪዝም፣ በግብርና፣ በኢነርጂ፣ በቴክኖሎጂ እና በማዕድን ዘርፍ በሰራነው ድምር ውጤት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተቋማቱ ግምት በአፍሪካ ከ9 በመቶ በላይ ዕድገት የምታረጋግጠው ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ ናት ብለዋል።
ተቋማቱ ኢትዮጵያ 9 ነጥብ 2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ታስመዘግባለች ብለው መተንበያቸውን ገልጸው፤ እኛ ከዚያም በላይ ዕድገት እንጠብቃለን ውጤቱን ሲደርስ የምናየው ይሆናል ነው ያሉት።
ውጤቱ የመጣው ግልጥ ያለ ስትራተጂ ኖሮን፣ የት ቦታ ምን ማድረግ እንደምንችል አውቀን፣ እንዴት መከታተል እንዳለብን ገብቶን በትጋት መስራት ስለቻልን ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የምትሰራው በአባቶቻችን ደም ብቻ ሳይሆን በእኛም ላብ እንደሆነም እናምናለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አባቶቻችን በደም ሀገር ሰርተው አቆይተዋል እኛ ደግሞ በላባችን ኢትዮጵያን መገንባት እንችላለን ብለዋል።
ከዚህ ውጪ ያለው አማራጭ እና አካሄድ እምብዛም አዋጭ እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።
ከአባቶቻንን ሲያስፈልግ ተዋግቶ ነጻነትን ማስጠበቅ ተምረን እኛም በተራችን በተግባር አሳይተናል ነው ያሉት።
ከአባቶቻችን በብዛት ያላየነውን በላብ፣ በደም፣ በፖሊሲ፣ በድካም ሀገር የመገንባት ሂደት ውስንነትን ማካካስ ተችሏል ሲሉ ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ብልጽግና ዓለም አፍሪካ በሚያምነው ልክ እየተረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።
ይህንን ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በአቢይ ጌታሁን