የሀገር ውስጥ ዜና

ሀሮ ደንዲ እና አካባቢው ኢትዮጵያን ያቆሙ ጀግኖች መፍለቂያ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Mikias Ayele

April 19, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀሮ ደንዲ እና አካባቢው ኢትዮጵያን ያቆሙ ጀግኖች መፍለቂያ እና ታሪካዊ አካባቢ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

በኦሮሚያ ክልል የገበታ ለትውልድ መርሐ ግብር አካል የሆነው የሀሮ ደንዲ ሎጅ ‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተመርቋል፡፡

‎ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የደንዲ ሐይቅ እና አካባቢው በተፈጥሮ ውበትና ጸጋ የታደለ ብቻ ሳይሆን የቀደመ ታሪኮችን የያዘ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የደንዲ ሐይቅ እና አካባቢው ከአስደናቂ ስፍራነቱ ባለፈ ኢትዮጵያን ያቆሙ እና ለኢትዮጵያ ዋጋ የከፈሉ ጀግኖች መናኸሪያ የሆነ አካባቢ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ለአብነትም የመጀመሪያው መከላከያ ሚኒስትር ሀብቴ አባመላ፣ በዓድዋ ጦርነት ጦር የመሩት ባልቻ ሳፎ (አባ ነፍሶ)፣ ሙሉጌታ ቡሊ፣ ጃገማ ኬሎ እና ገረሱ ዱኪ የአካባቢው ተወላጆች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የእነዚህን ጀግኖች ታሪክ መዘከር እና ማሳየት የሚቻለው እንደነዚህ አይነት ቦታዎች አብረው ሲገለጡ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡

ኢትዮጵያ ታሪክ እና እምቅ የቱሪዝም ሀብት አላት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን ሀብት በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል መሰረተ ልማት ግን አልነበራትም ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት ከመንግስት በጀት ውጪ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ እንደ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ አይነት ፕሮጀክቶችን መገንባት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

ባለሀብቱን በማስተማር እና በማስተባበር በተሰራው ስራ እንደ ወንጪ ደንዲ፣ ሸበሌ ሪዞርት፣ የቤኑና መንደሮች፣ ጉርጎራ፣ ሀላላ ኬላ፣ ጨበራ ጩርጩራ እና ሌሎች የገበታ ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን አብራርተዋል።

በሚኪያስ አየለ