አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያና ብሪታኒያ የኢንቨስትመንትና የልማት ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ከሚገኘው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) እና ዓለም ባንክ የጸደይ ወቅት ስብሰባ ጎን ለጎን ከብሪታኒያ የዓለም አቀፍ ልማት ሚኒስትር ዴዔታ ባሮነስ ቻፕማን ጋር ተወያይተዋል፡፡
አቶ አህመድ ሺዴ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን ጠንካራ የተሃድሶ ግስጋሴ እና አዎንታዊ የኢኮኖሚ እይታ ገልጸው፤ የተሀድሶ ግኝቶችን ለማስቀጠል ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
ባሮነስ ቻፕማን በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያን የለውጥ እንቅስቃሴ እና መሻሻሎችን አድንቀው ብሪታኒያ ለልማት ትብብር ያላትን ቀጣይ ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋትን በማስፈን ረገድ ኢትዮጵያ ያላትን ጠቃሚ ሚና አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች ከልማት ትብብር ባለፈ ጠንካራ የንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና ኢኮኖሚያዊ ትብብራቸውን ለማስፋት ተስማምተዋል።