አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያና አሜሪካ ያላቸውን ኢኮኖሚያዊ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ተስማምተዋል።
በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የተመራ ልዑክ በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ካለው የ2026 የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) እና ዓለም ባንክ የጸደይ ወቅት ስብሰባ ጎን ለጎን ከአሜሪካ የግምጃ ቤት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ማሳደግ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ምክክር ተደርጓል።
እንዲሁም ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው እንደ ቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ያሉ ትላልቅ የልማት ስራዎች ላይም ተወያይተዋል።
በዚህም ሁለቱም ወገኖች የጋራ የኢኮኖሚ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በማስቀደም የኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣትና ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል።
የአሜሪካ መንግሥት ኃላፊዎች በበኩላቸው የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሂደት በማድነቅ፤ በቴክኒክ፣ በግል ዘርፍ ተሳትፎና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመተባበር ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።