ፋና ስብስብ

ዓለምን ያስደመመው ኢትዮጵያዊ ዲዛይነር

By Adimasu Aragawu

April 20, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እድሜን የጠገቡ፣ የመጀመሪያ ገጽታቸውን ከእርጅና ብዛት የረሱ፣ ከላይም ከታችም የተቀደዱ እና ከመወየብ ያለፉ፣ አቧራ ከመጠጣት ብዛት ቀለማቸውን የቀየሩ ልዩ ልዩ ጫማዎች እና ቦርሳዎች በአንድ ብሎኬት ግድግዳ ላይ ተደርድረው ይታያሉ።

በዚህ ለዓይን የሚስብ ነገር የሌለበት በሚመስል እና የኮተታ ኮተት ስብስብ በሆነ ግድግዳ ፊት ታዲያ አንድ ኢትዮጵያዊ ታዳጊ ወጣት ዓለምን ያስደነቀ፣ የፋሽን ዲዛይነሮችን ቀልብ የሳበ፣ በርካቶችን ማነጋገር ችሏል።

ስሙ ካሌብ ወይም (Kalu Putik) ይባላል፤ ከወዳደቁ ቁሳቁሶችን የተሰሩ አልባሳትን በመልበስ አጫጭር ቪዲዮዎችን የሚሰራ ሲሆን በተለያዩ የማሕበራዊ ሚዲያ መድረኮች በሚሊየኖች ዘንድ ይታወቃል።

ሌሎች የጣሏቸውን የጎማ ቁርጥራጮች፣ ያረጁ ጨርቆች፣ ካርቶን እና ፕላስቲኮችን በመጠቀም የሚሰራቸው የፋሽን ሥራዎችን በማሕበራዊ ሚዲያ መድረኮች ያስተዋውቃል።

በዚህም ውድ ጨርቆች፣ ዘመናዊ የስፌት ማሽኖች ወይም የፋሽን ዲዛይን ትምህርት ሳይኖረው በዙሪያው የሚያገኛቸውን የወዳደቁ አልባሳትን ወደ ጥበብ ሥራነት እየቀየረ ይገኛል።

እነዚህን አልባሳት እየለበሰ በሚሰራቸው አጫጭር ቪዲዮዎች ከመላው ዓለም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተከታይ ማፍራት የቻለ ሲሆን፤ በቲክቶክ ከ700 ሺህ በላይ እንዲሁም በኢንስታግራም ከ560 ሺህ በላይ ተከታዮችን አፍርቷል።

አጫጭርና ተመልካችን የሚስቡ ቪዲዮዎቹ የቋንቋ እና የቦታ ገደብን ሰብረው የዓለምን ትኩረት መሳብ የቻለው ካሌብ በዚህ የዲጂታል ዘመን የፋሽን ዲዛይን ትኩረት ማዕከል መሆን ችሏል።

ወጣቱ ካሌብ አሜሪካዊቷን አቀንቃኝ ኤስዜኤን (SZA) ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ አርቲስቶች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እና ድርጅቶች አድናቆታቸውን እየገለጹለት ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪ በፋሽኑ ዓለም ላይ የተሰማሩ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ለሥራዎቹ አድናቆታቸውን እያጎረፉለት እና እያበረታቱት ሲሆን፤ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም የዘገባ ሽፋን እየሰጡት ነው።

የካሌብ ስኬት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የዲጂታል ፈጠራ አቅም የሚያሳይ ሲሆን ከማህበራዊ ሚዲያ ዝና ባለፈ ኢትዮጵያን በችሎታ እና በፈጠራ እንድትታወቅ እያደረገ ነው።

አሁን ላይ ከኢትዮጵያ ባሻገር በዓለም አቀፍ መድረክ ዕውቅናን እያገኘ የሚገኘው ካሌብ፤ ወደፊት ከትላልቅ የፋሽን ኩባንያዎች ጋር አብሮ የመስራትና የራሱን አሻራ በዓለም ላይ የማሳረፍ ሰፊ እድል እንዳለው ይጠበቃል።

በዮናስ ጌትነት