ቢዝነስ

ኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት የኢኮኖሚ አጋርነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

By sosina alemayehu

April 20, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ አጋርነታቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል።

በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የተመራ ልዑክ በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ካለው የ2026 የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) እና ዓለም ባንክ የጸደይ ወቅት ስብሰባ ጎን ለጎን ከአውሮፓ ኅብረት የዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ጆሴፍ ሲኬላ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርጓል።

ውይይቱ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግና በኢኮኖሚ ትብብር ላይ አዲስ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ነው።

በዚህም የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመደገፍ ፣ የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ይበልጥ ለማሻሻል፣ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም በሚያስችሉ ስራዎች እና ቀጣይነት ባለው የኢኮኖሚ እድገት ግቦች ላይ በትብብር ለመስራት አቅጣጫ ተቀምጧል።

እንዲሁም ሁለቱም ወገኖች ያላቸውን የቆየ አጋርነት በማደስ፣ ትብብራቸውን ወደ ተጨባጭ እና ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ወዳላቸው ውጤቶች ለመቀየር ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

ስምምነቱ በኢትዮጵያና በአውሮፓ ኅብረት መካከል ያለውን የቆየ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግርና ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት የላቀ ሚና የሚጫወት መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።