አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) የልማት አጋርነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ተስማምተዋል።
በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የተመራ ልዑክ በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ካለው የ2026 የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) እና ዓለም ባንክ የጸደይ ወቅት ስብሰባ ጎን ለጎን ከጃይካ ምክትል ፕሬዚዳንት ናኦኪ አንዶ ጋር ተወያይቷል።
አቶ አህመድ ሺዴ ኢትዮጵያ ከጃፓን ጋር ያላት ረጅም ዘመናት ያስቆጠረ አጋርነት የሚደነቅ መሆኑን አንስተው፤ በተለይም ጃይካ በመሰረተ ልማት፣ በግብርና፣ በጤና እና በትምህርት ዘርፎች ለሚያደርገው ቀጣይነት ያለው ድጋፍ አመስግነዋል።
ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለውን የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ አፈፃፀም በተመለከተ ገለጻ ያደረጉት ሚኒስትሩ፤ በዓለም አቀፍ ፈተናዎች መካከል የታየውን የኢኮኖሚ ጥንካሬ በተመለከተ አብራርተዋል።
ጃይካ በአቪዬሽን፣ በኃይል አቅርቦት እና በመንገድ መሰረተ ልማት ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዘርፎች ላይ ድጋፉን እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን በማሳደግ እና በአረንጓዴ ልማት ስራዎች ላይ ጃይካ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ናኦኪ አንዶ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን የልማት አጀንዳ ለመደገፍ ቁርጠኝነት መኖሩን አረጋግጠዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ቅድሚያ በሚሰጣቸው የጋራ ጉዳዮች ላይ ያለውን ትብብር እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።