የሀገር ውስጥ ዜና

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሶስት ረቂቅ ደንቦችን አጸደቀ

By sosina alemayehu

April 21, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ዛሬ ባካሄደው 5ኛ ዓመት 10ኛ መደበኛ ስብሰባ በሶስት ረቂቅ ደንቦች ላይ ተወያይቶ ተፈጻሚ እንዲሆኑ አጽድቋል።

በስብሰባው በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ ከተወያየ በኋላ ሶስት ረቂቅ ደንቦች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ውሳኔ አስተላልፏል።

በዚህም የተሻሻለ የፋይናንስ አስተዳደርን ይበልጥ ለማዘመን፣ ተጠያቂነትንና የአሰራር ግልፀኝነትን ለማጎልበት የተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ተፈጻሚ እንዲሆን ወስኗል።

እንዲሁም በከተማዉ እየተገነባ ያለው ሰፊ የቤት ልማት የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖረው፣ የቤቶች ኮርፖሬሽን ሪፎርምን ለማጠናከር እና የማስፈፀም ብቃት ለማሳደግ የተዘጋጀዉን ረቂቅ ደንብም አፅድቋል።

የመሬት ማስፋፍያ ለጠየቁ ተኪ ምርት ለሚያመርቱ ኢዱስትሪዎች፣ ለወጣቱ የስራ ዕድል የፈጠሩ ፕሮጀክቶች፣ ሆቴሎች እንዲሁም፥ በከተማ አስተዳደሩ ከሐይማኖት ተቋማት ጋር በተደረጉ ተከታታይ ውይይቶች የተነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መፍታት የሚያስችል መሬት በምደባ ለማስተላለፍ የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ተፈፃሚ እንዲሆን በስብሰባው ወስኗል።