አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተሰሩ የሪፎርም ስራዎች ተጨባጭ ውጤት አምጥተዋል አሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የ100 ቀናት ግምገማ እና የ9 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ቀርቧል።
ሚኒስትሯ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳብራሩት፤ የእኛን ተጨባጭ ሁኔታ የሚመስል ሀገራችንን፣ ሕዝባችንን እና ሀብታችንን መሰረት ያደረገ ሰፊ የሪፎርም ስራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
በዚህም የመንግሥት ሚና እንደ አዲስ ተቃኝቷል ያሉት ሚኒስትሯ መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ ህግ ከማውጣትና ከማስከበር ባለፈ ከግሉ ዘርፍ ጋር በትብብር እንዲሰራ አድርጓል ብለዋል፡፡
ሁለት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መቀረጻቸውን ጠቅሰው፤ ሁለተኛው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በዚህም ትልቅ የኢኮኖሚ እይታ ለውጥ መምጣቱን አንስተው፤ ሪፎርሙ በውጤት የሚገለጽ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል ነው ያሉት፡፡
ጥራት ያለው ኢኮኖሚ የሚያስመዘግቡ፣ ምርታማነትን የሚጨምሩ እና የስራ ዕድል የሚፈጥሩ ዘርፎች ላይ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን አብራርተዋል፡፡
ዘላቂ የሆነ የልማት ፋይናንስ በተሳካ ዲፕሎማሲያዊ ድርድር ማምጣት መቻሉን ጠቁመው፤ ይህም ልማታችንን በተሻለ እንድንፈጽም አስችሎናል ብለዋል፡፡
ባለፉት ስምንት ዓመታት መንግሥት አንድም ዶላር እንዳልተበደረ ገልጸው፤ አዳዲስ የፋይናንስ አማራጮች ጥቅም ላይ መዋላቸውን አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዘመናዊነት የበለጠ ጠንካራ የሚያደርግ የካፒታል ገበያ ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰው፤ ኢኮኖሚው ተፈጥሯዊ ዕድገቱን ጠብቆ እየሄደ ነው ብለዋል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ