አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ጋር ስኬታማ ዓመታትን ማሳለፍ የቻለ ኮከብ ነው ብራዚላዊው ተጫዋች ዴቪድ ሉዊዝ፡፡
የብራዚል ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ተጫዋች ዴቪድ ሉዊዝ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ሕይወቱን የጀመረው በሀገሩ ክለብ ቪቶሪያ ነው፡፡
የቼልሲ የቀድሞ ኮከብ በዓለም እግር ኳስ ከታዩ ምርጥ የመሐል ተከላካዮች መካከል አንዱ ሲሆን ከአስደናቂ የመከላከል ብቃቱ ባለፈ በሚያስቆጥራቸው የቅጣት ምት ግቦች ይታወቃል፡፡
ከሀገሩ ክለብ ቪቶሪያ በኋላ የፖርቹጋሉን ክለብ ቤኔፊካ በመቀላቀል ለአምስት የውድድር ዓመታት ቆይታ አድርጓል፡፡
ከቤኔፊካ ጋር በ2009/10 የውድድር ዓመት የፖርቹጋል ሊግ ዋንጫን ያሳካው ዴቪድ ሉዊዝ በዚያው የውድድር ዓመት የሊጉ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ መመረጡ ይታወሳል፡፡
ከፖርቹጋሉ ክለብ ቤኔፊካ ጋር ጥሩ የውድድር ጊዜያትን ካሳለፈ በኋላ በ2010/11 የውድድር ዘመን የምዕራብ ለንደኑን ክለብ ቼልሲ መቀላቀል ችሏል፡፡
በቼልሲ በነበረው የመጀመሪያ ዙር አራት የውድድር ዓመታት ቆይታ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ፣ ዩሮፓ ሊግ እና የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡
ዴቪድ ሉዊዝ በዋንጫ የታጀቡ አራት የውድድር ዓመታትን በቼልሲ ካሳለፈ በኋላ የፈረንሳዩን ክለብ ፒኤስጂን በ50 ሚሊየን ፓውንድ መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡
ፒኤስጂ ዴቪድ ሉዊዝን ለማስፈረም ወጪ ያደረገው 50 ሚሊየን ፓውንድ በወቅቱ የተከላካዮች የዝውውር ክብረ ወሰን ነበር፡፡
ተጫዋቹ በፈረንሳዩ ክለብ ፒኤስጂ በቆየባቸው ሦስት የውድድር ዓመታት የፈረንሳይ ሊግን ጨምሮ የተለያዩ ዋንጫዎችን ማሳካት ችሏል፡፡
በ2016/17 የውድድር ዓመት በድጋሚ ወደ እንግሊዙ ክለብ ቼልሲ በ30 ሚሊየን ፓውንድ ተመልሷል፡፡
ዴቪድ ሉዊዝ በቼልሲ በነበረው የሁለተኛ ዙር ቆይታ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ፣ ኤፍ ኤ ካፕ እና የዩሮፓ ሊግ ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡
ተጫዋቹ በምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ የሁለተኛ ዙር ቆይታውም የተሳካ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ ሌላኛውን የእንግሊዝ ክለብ አርሰናልን በ2019 መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡
ዴቪድ ሉዊዝ በአርሰናል በቆየባቸው ሁለት የውድድር ዓመታት የኤፍ ኤ ካፕ እና የኮሚኒቲ ሺልድ ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡
ከአርሰናል በኋላ ለሀገሩ ክለቦች ፍላሚንጎ እና ፎርቴላዛ መጫወት የቻለ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለፓፎስ እየተጫወተ ይገኛል፡፡
ለሀገሩ ብራዚል ከፈረንጆቹ 2010 ጀምሮ እስከ 2017 ያገለገለው ዴቪድ ሉዊዝ ለብሔራዊ ቡድኑ 57 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡
ዴቪድ ሉዊዝ ሀገሩ ብራዚል በፈረንጆቹ 2014 ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ውድድር ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር እስከ ግማሽ ፍጻሜ መጓዙ ይታወሳል፡፡
በወቅቱ ብራዚል ከውድድሩ ስትሰናበት ዴቪድ ሉዊዝ ፊት ላይ የታየው የሀዘን ስሜት በስፖርት ቤተሰቦች ዘንድ የሚረሳ አይደለም፡፡
የቼልሲ የቀድሞ የተከላካይ ሥፍራ ተጫዋች ዴቪድ ሉዊዝ በፈረንጆቹ 1987 በዛሬዋ ዕለት ነው የተወለደው፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ