የሀገር ውስጥ ዜና

የአሜሪካ መንግስት ተቋማት ለቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ…

By Adimasu Aragawu

April 22, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ከአሜሪካ የመንግሥት ተቋማት፣ ከዋና ዋና የፋይናንስ ተቋማት እና ከታዋቂ ኩባንያዎች ከፍተኛ ድጋፍ አግኝታለች።

ተቋማቱ በዋሽንግተን የፋይናንስ ሮድሾው መድረክ ላይ ለፕሮጀክቱ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የገለጹ ሲሆን÷ ድጋፉም በአፍሪካ ግዙፍ ከሚባሉ የአቪዬሽን መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነውን የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዕውን ለማድረግ የተወሰደ ወሳኝ ርምጃ መሆኑ ተገልጿል።

ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናትም በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ እና እድገት ላይ ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ በዚህ ወቅት÷ አውሮፕላን ማረፊያው ለንግድ እና ኢንቨስትመንት እንደ ማነቃቂያ እንደሚያገለግል ተናግረዋል።

እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በማጠናከር ረገድ እንደ ትልቅ ምሰሶ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን ጠቅሰው÷ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሪፎርም ከመደገፉም በላይ ለአሜሪካ ኩባንያዎች ሰፊ የንግድ ዕድሎችን እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው÷ ፕሮጀክቱ ከአሜሪካ ተቋማት ጋር ያለውን የቆየ አጋርነት በማጠናከር እያደገ የመጣውን የዓለም አቀፍ ትራንስፖርት ፍላጎት ለማርካት እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

የፕሮጀክቱ ዋና የፋይናንስ አስተባባሪ በሆነው የአፍሪካ ልማት ባንክ የፋይናንስ ምክትል ፕሬዚዳንት ሀሳቱ ሴሌ የፕሮጀክቱን አዋጭነት እና አህጉራዊ ፋይዳ ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል።

በገለጻቸውም ፕሮጀክቱ ጠንካራ መሠረት ያለው፣ አዋጭ እና ከፍተኛ ተፅዕኖ ያለው መሆኑን ገልጸው÷ ቀጣናዊ ትስስርን ከማጠናከር ባሻገር ተወዳዳሪነትን እንደሚጨምርና በመላው አፍሪካ ዘላቂ እድገትን እንደሚያፋጥን አብራርተዋል።