የሀገር ውስጥ ዜና

በለውጡ የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት በተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል – አቶ አዲሱ አረጋ

By Adimasu Aragawu

April 22, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት የለውጥ ዓመታት ግብርናን ከባህላዊ አስተራረስ ወደ ሜካናይዜሽን ለማሸጋገር በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል አሉ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ፡፡

የ2018 በጀት ዓመት ሶስተኛው የ100 ቀናት እና የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።

አቶ አዲሱ አረጋ መድረኩን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ÷ ከለውጡ በፊት የግብርና ማሽነሪዎችን የሚያበረታታ ፖሊሲ እንዳልነበር አስታውሰዋል።

በዚህ ምክንያትም ከቀረጥ ነጻ የማስገባት፣ ለአርሶ አደሮች በብድር የማቅረብ እንዲሁም የሰው ሃይል ስልጠና ትኩረት ባለማግኘቱ የእርሻ ማሽነሪዎች ቁጥር አነስተኛ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

በአንጻሩ በለውጡ መንግሥት የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማጠናከር በተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል ነው ያሉት።

አሁን ላይ ከ27 ሺህ በላይ ትራክተሮች፣ ከ8 ሺህ በላይ ኮምባይነሮች እንዲሁም ከ280 ሺህ በላይ በሞተር የሚሰሩ የውሃ ፓምፖች መኖራቸውን አብራርተዋል።

ይህም የግብርና ዘርፉ ከዘልማድ አሰራር በመላቀቅ ወደ ሜካናይዜሽን እየተሸጋገረ እንደሆነ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የግብርና ሜካናይዜሽን ሥራ የ72 ከመቶ አድገት ማሳየቱንም አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ በትራክተር የሚለማው መሬት ወደ 7 ሚሊየን የተጠጋ ሲሆን ፥ ይህም ከሚለማው መሬት አንድ ሶስተኛው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የግብርና ዘርፉን ከዝናብ ጠባቂነት ወደ መስኖ ልማት ለማሸጋገር የተከናወነው ሥራ ውጤታማ መሆኑን ነው የገለጹት።

በግብርና ዘርፍ በተካሄደው ትራንስፎርሜሽን የምርት እድገት መጨመሩ እና የአርሶ አደሩ ሕይወት መሻሻሉንም አቶ አዲሱ አስገንዝበዋል፡፡

በአቤል ነዋይ