አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም) የኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በቱሪዝም ዘርፍ ባከናወነቻቸው ሥራዎች አስደናቂ ለውጦች እየተመዘገቡ ይገኛሉ።
ታሪካዊ፣ ባሕላዊና ተፈጥሯዊ ጸጋዎችን ከዘመናዊ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ጋር በማቀናጀት ኢትዮጵያን ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ማራኪ መዳረሻ እንድትሆን ያስቻሉ የቱሪዝም ልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው።
ብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚን እየተገበረች የምትገኘው ኢትዮጵያ ቱሪዝምን ከአምስቱ የኢኮኖሚ ዓምዶች መካከል አንዱ በማድረግ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች፡፡
በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት የተተገበሩ የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ መርሐ ግብሮች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲስፋፉ አድርገዋል።
የአዲስ አበባን ገጽታ መቀየር ያስቻሉ የአንድነት፣ እንጦጦ እና ሸገር ፓርኮች እንዲሁም የሳይንስ ሙዚየምን የመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ከተማዋ ለጎብኚዎች ተስማሚና ምቹ እንድትሆን አድርገዋል።
የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልን ጨምሮ የኮሪደር ልማት እንዲሁም የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች የከተማዋን እምቅ የኮንፍረንስ ቱሪዝም አቅም በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር አስችለዋል።
በተለያዩ ክልሎች የተገነቡት እንደ ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ኮይሻ፣ ቤኑና፣ ሀሮ ደንዲ እና ደንቢ ኢኮ ሎጅ ያሉ መዳረሻዎች የኢትዮጵያን የቱሪዝም አድማስ በከፍተኛ ደረጃ ለማስፋት ያስቻሉ ናቸው።
እንዲሁም ዘርፉን ዲጂታላይዝ በማድረግ የቱሪስት መዳረሻዎች በተመለከተ መረጃዎችን በድረገጽ ለማግኘት የሚያስችል “ቪዚት ኢትዮጵያ” የተሰኘ የዲጂታል ፕላትፎርም ወደ ስራ መግባቱ የሚታወስ ነው።
በእነዚህ የልማት ሥራዎች ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት 9 ወራት ብቻ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ተቀብላ ማስተናገድ የቻለች ሲሆን፥ ከዚህም ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች።
ከዓለም አቀፍ ጎብኚዎች በተጨማሪ ከሀገር ውስጥ ቱሪዝም ብቻ በተመሳሳይ 60 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ገቢ ማግኘት ተችሏል።
ኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ ረገድ ላሳየችው ጥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ እውቅናዎችን ማግኘት ችላለች፡፡
ለአብነትም የተባበሩት መንግሥታት የቱሪዝም ማዕከል ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2025 እና 2026 በዓለም ፈጣን የቱሪዝም እድገት እያሳዩ ከሚገኙ ሀገራት መካከል በመመደብ ዕውቅና ሰጥቷል።
በተመሳሳይ የዓለም የጉዞና የቱሪዝም ምክር ቤት ኢትዮጵያ በ2025 ያስተናገደቻቸው ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ቁጥር እድገት እንደታየበት ጠቅሶ፥ በ2025 ተስፋ ሰጪ የቱሪዝም መዳረሻዎች አንዷ መሆኗን አመልክቷል።
እንዲሁም በዓለም የጉዞ ሽልማት በ2025 እና 2026 ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ መዳረሻ ዘርፍ መታጨት የቻለች ሲሆን፥ እነዚህ ስኬቶችና በዘርፉ የተፈጠረው መነቃቃት በዋናነት የአመራር ቁርጠኝነትና የቅርብ ክትትል ውጤት መሆናቸው ይታመናል፡፡
የግል ባለሀብቶችን በስፋት በማሳተፍና በዘርፉ የተገኙ ውጤቶችን ይበልጥ በማጠናከር ቱሪዝምን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተሰራ ይገኛል።
በዮናስ ጌትነት