የሀገር ውስጥ ዜና

 የመማር ማስተማር ሂደት በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By Mikias Ayele

April 24, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመማር ማስተማር ሂደት በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡

ከንቲባዋ “በሳይንስና ፈጠራ የተካነ ትውልድ ለተምሳሌታዊ ሀገር”  በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄደውን 11ኛ ከተማ አቀፍ የተማሪዎች የፈጠራ አውድ ርዕይ በዛሬው ዕለት አስጀምረዋል።

ከንቲባ አዳነች በዚህ ወቅት÷ የመማር ማስተማር ስራዎችን በቴክኖሎጂ የተደገፉ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

መምህራንና ተማሪዎች ለኢትዮጵያ ብልጽግና ዐሻራቸውን እያኖሩ ይገኛሉ ያሉት ከንቲባዋ÷ በዚህም የፈጠራ ሥራዎችን የበለጠ በማስተማርና የውድድር መንፈስን በመፍጠር ከተማዋን ስማርት ሲቲ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ሚናቸውን መጫወት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በአውድ ርዕዩ የቀረቡ የፈጠራ ስራዎች ተስፋ የሚሰጡና የሚያበረታቱ መሆናቸውን በመግለጽም ትምህርት ቢሮው መሰል የፈጠራ ስራን የሚያበረታቱ ተግባራትን አጠናክሮ እንዲቀጥል ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የመፍጠርና የመፍጠን አሰራርን የሚከተል አመራር እየተገነባ መሆኑን ጠቅሰው÷ ይህም የፈጠራ ክህሎት ላላቸው መምህራንና ተማሪዎች ምቹ አጋጣሚ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ ሀገር ከሐሳብ ባለፈ በእውቀት የመተግበር አቅም ያለው ትውልድ ለመገንባት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው÷ ይህም ለሳይንስ ፈጠራ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የእድገት ጉዟችን የብልጽግናችንን መዳረሻ አመላካች ቃልኪዳን እንጂ መድረክ ብቻ አይደለም ብለዋል።

የፈጠራ ስራና ምርምር ለማሳደግ የተወሰደው ቁርጠኝነት እያንዳንዱ ተማሪ እውቀት ብቻ ሳይሆን አመለካከትን ወደ ተግባር እንዲቀይር እያስቻለ መምጣቱን አረጋግጠዋል።

ተማሪዎች በንድፍ ሐሳብ የተማሩትን ወደ ተግባር ለመቀየርና የፈጠራ ክህሎት ያላቸው የሚበረታቱበት አሰራር በትምህርት ቤቶች እየተተገበረ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ዐውደ ርዕይ ከ5ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚማሩ ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንደየክፍል ደረጃቸው በተለያዩ ዘርፎች የፈጠራ ስራዎቻቸውን እያቀረቡ መሆናቸውም ተገልጿል።

በግዛቸው ግርማዬ