ቴክ

ቻይና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ስርቆት ከአሜሪካ የቀረበባትን ክስ አጣጣለች

By Abiy Getahun

April 24, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ቻይና በተደራጀ መልኩ የአሜሪካን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ለመስረቅ ጥረት አድርጋለች የተባለውን ክስ መሰረተ ቢስ ስትል ውድቅ አድርጋለች።

የነጩ ቤተ መንግስት የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኃላፊ ሚካኤል ክራቲሲዮስ ትናንት በኤክስ ገጻቸው ቻይና የተቀናጀ የስርቆት ጥረት ማድረጓን በመጥቀስ፤ አሜሪካ ፈጠራዎቿን ለመጠበቅ ርምጃ እንደምትወስድ አስጠንቅቀው ነበር።

ይህንን ተከትሎ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጉዎ ጂያኩን የአሜሪካ ክስ ሙሉ በሙሉ መሠረተ ቢስ ነው ብለዋል።

ቻይና በዘርፉ ያስመዘገበችውን ውጤት ለማጠልሸት የተደረገ ስም ማጥፋት በመሆኑ በጽኑ እንቃወማለን ሲሉ ተናግረዋል።

አሜሪካ እውነታውን መቀበል እና ቴክኖሎጂን በብቸኝነት እንቆጣጠር የሚለውን ሃሳብ መተው አለባት ነው ያሉት።

ከዚህ ይልቅ በሀገራቱ መካከል የቴክኖሎጂ ልውውጥን እና ትብብርን የበለጠ ማሳደግ ይገባል ማለታቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

ቻይና ክሱን ውድቅ ያደረገችው ከዓመት በፊት ዓለምን ያነጋገረው የቻይናው “ዲፕ ሲክ” አዲስ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሞዴል ይፋ ካደረገ በኋላ ነው።

ከአሜሪካዎቹ የሰው ሰራሽ መተግበሪያዎች እጅግ ባነሰ ወጪ የተሰራው “ዲፕ ሲክ” በሚል የሚታወቀው የቻይናውያን የፈጠራ ውጤት በመላው ዓለም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቀባይነትን በማግኘት መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበር ይታወሳል።

በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ዲፕ ሲክ” ለአሜሪካውያን የማንቂያ ደውል ነው ማለታቸው ይታወሳል።

በብርሃኑ አበራ