አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም) የፍትህ ስርዓቱን ውጤታማነት በማሳደግ በሀገር ላይ የመጡ ዓለም አቀፍ ክሶችን መቀልበስ ተችሏል አሉ የፍትህ ሚኒስትር ሀና አርዓያሥላሴ።
የ2018 በጀት ዓመት ሦስተኛው የ100 ቀናት እና የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።
መድረኩን አስመልክቶ የፍትህ ሚኒስትሯ በሰጡት ማብራሪያ፤ የፍትህ ስርዓቱን ቅልጥፍና እና ውጤታማነት ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
የፍትህ ዘርፉ ከለውጡ በፊት መሰረታዊ የሚባሉ ችግሮች እንደነበሩበት አስታውሰው፤ ባለፉት ስምንት ዓመታት ይህንን ለመቅረፍ በርካታ የሕግ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል።
ማሻሻያው በተቋማት ውስጥ ከአደረጃጀት እና ከአሰራር ጀምሮ ያለው ሂደት በሕግ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አስችሏል ነው ያሉት።
የፍትህ ተደራሽነትን ከማሳካት አንጻር ባህላዊ የፍርድ አሰጣጥ ሂደቶች በሕግ እውቅና እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉ አንዱ ተጠቃሽ ስኬት ነው ብለዋል።
ባህላዊ የፍርድ አሰጣጥ ሂደቶች የፍትህ ተደራሽነትን በማሳካት ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑን አንስተው፤ በፌደራልና በክልል ያሉ ተቋማትን ለማቀናጀት በተሰራው ሥራ ትላልቅ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።
አዲስ የፍትህ ስትራቴጂ በማውጣት ወደ ሥራ መገባቱን እና በወንጀል ፍትህ አስተዳደሩ ላይ የመጣውን ለውጥ በማሳያነት ጠቅሰዋል።
እንዲሁም በሀገር ላይ የሚመጡ ክሶችን በውጤታማነት መቀልበስ ተችሏል ብለዋል።
ከእነዚህም መካከል የ350 ሚሊየን ዶላር ተጠያቂነት ይዞ የመጣ ጉዳይን ሙሉ በሙሉ መመከት የተቻለበት ሁኔታ እንዳለና ይህም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ትልቅ ስኬት መሆኑን አስረድተዋል።
በሶስና አለማየሁ