አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የራስ ኃይሉ የስፖርት፣ ትምህርትና ስልጠና ማዕከል ተጨማሪ መሰረተ ልማቶች ተሟልቶ ወደ አገልግሎት እንዲገባ አደረጉ።
ከንቲባ አዳነች በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ ማዕከሉን ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማካሄድ በሚያስችል ደረጃ በማደስ እና ተጨማሪ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ወደ አገልግሎት እንዲገባ አድርገናል ብለዋል።
ማዕከሉን ቀደም ብሎ መርቀን አገልግሎት መስጠት ካስጀመርን በኋላ ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ምክንያት አገልግሎቱ ተቋርጦ መቆየቱን አመላክተዋል።
የቴክኒክ ችግሩ እንዲፈታ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን እንዲያሟላ የሚያስችሉ ተጨማሪ መሰረተ ልማቶች እንዲካተቱለት በማድረግ አገልግሎቱን በድጋሚ እንዲጀምር አድርገናልም ነው ያሉት ከንቲባዋ በመልዕክታቸው።
ዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ስታንዳርድን የተጠበቀ የመዋኛ ገንዳዎች፣ ሁለገብ ጅምናዚየም፣ የቅርጫት ኳስ፣ የእጅ ኳስ፣ የቮሊ ቦል፣ የቦክስ፣ የማርሻል አርት ውድድሮችን ማካሄድ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች፣ የሚዲያ ማዕከል፣ የቴኒስና የእግር ኳስ ሜዳዎች፣ ካፍቴሪያ እና ሱቆችን እንዲሁም መናፈሻ እና የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎችን አካቶ የያዘ ዘመናዊ የስፖርት ማዕከል ነው ብለዋል።
በአካልም በአዕምሮም ዳብሮ የተገነባ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለመገንባት በሰነቅነው ራዕይ በከተማችን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን እና የስብዕና መገንቢያ ማዕከላትን በማስፋፋት ህጻናት እና ታዲጊዎች ስልጠናዎችንና ልምምዶችን እንዲያገኙ በስፖርት የዳበሩ፣ ጤናቸው የተጠበቀ እና ተወዳዳሪ ብሎም አሸናፊ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋልም ያሉት።
ማዕከሉ ከዛሬ ጀምሮ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን፣ ልምምዶችን እና ስልጠናዎችን ጨምሮ በተሟላ መልኩ አገልግሎት መስጠት የጀመረ በመሆኑ ተገልገሉበት፣ ጠብቁት፣ ተንከባከቡት ሲሉም አሳስበዋል።