የሀገር ውስጥ ዜና

የሀገራዊ ምክክሩ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተጠናቅቆ ዋናውን ጉባኤ ለማካሄድ የመጨረሻው ዝግጅት እየተከናወነ ነው – መስፍን አርዓያ (ፕር)

By Adimasu Aragawu

April 25, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገራዊ ምክክሩ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተጠናቅቆ ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለማካሄድ የመጨረሻው ዝግጅት እየተከናወነ ነው አሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕር)።

ዋና ኮሚሽነሩ እንዳሉት÷ ሀገራዊ ምክክሩ ለዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሰረት የሚጥል ነው፡፡

ምክክሩ ዜጎች በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ በመድረስ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ዘላቂ ልማትና ዕድገት ማስመዝገብ የሚችሉበትን ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

የሐሳብ ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ በንግግር መፍታት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው÷ ዜጎች በሀገራዊ ምክክሩ የተፈጠረው ዕድል በመጠቀም ለሀገራቸው ሰላምና ልማት ገንቢ ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በምክክር ሂደቱ በክልላቸውና በሀገራቸው ያሉ ችግሮችን ነቅሰው በማውጣት ለኮሚሽኑ ማቅረባቸውንም አስታውሰዋል፡፡

በሁሉም ክልሎች፣ በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ምክክር መካሄዱን ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይ ሳምንታት በሀገር አቀፍ ደረጃ 170 ለሚደርሱ የተመረጡ አማካሪዎች ስልጠና እንደሚሰጥ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በሀገራዊ ምክክሩ ጉባኤው የሚሳተፉ ዜጎች ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል የሚወክሉ መሆናቸውን ገልጸው÷ ዋና ጉባኤውን ለማካሄድም የመጨረሻ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ፣ እንደ ሀገር በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር በኩል በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱ ይታወቃል።