አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጸጋዎቿን ወደ ኃይል ለመቀየር በርካታ ስራዎችን እየሰራች ትገኛለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል እንድትሆን በንጹህና ታዳሽ ኃይል ላይ እየተሰራ እንደሚገኝና በበቂ ደረጃ ኃይል ማምረት ለኢንዱስትሪ ወሳኝ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።
በዚህም የታዳሽ ኃይል ምንጮችን ማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ሲሆን÷ በተለይም የነፋስ ኃይልና የጸሐይ ኃይል ማመንጫዎችን ጨምሮ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት ወደ ኃይል ለመቀየር እየተሰራ ይገኛል።
እያደገ ከሚገኘው የኢንዱስትሪ ዘርፍና ተያይዞ ከሚመጣው የኃይል ፍላጎት እድገት ባሻገር ለጎረቤት ሀገራት የኃይል ሽያጭ በማቅረብ ቀጣናውን የማስተሳሰር ሥራን እያከናወነች የምትገኘው ኢትዮጵያ÷ ይህንን በአግባቡ ለማከናወን የኃይል ምንጮችን ማብዛት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው።
በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ሰፊ ቦታ የሚይዘውን የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ዘርፍ ለማሳደግ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ መግባ ከፍተኛ አቅም መፍጠር ችሏል።
በተጨማሪም 1 ሺህ 800 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለውን የኮይሻ ኃይል ማመንጫን አጠናቅቆ ወደ ሥራ ለማስገባት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።
ከኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ባሻገር በሚገኙ የታዳሽ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት በማድረግም በርካታ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ።
በነፋስ ኃይል ማመንጫ ዘርፍ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሜጋ ዋቶችን ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት እየጨመሩ ከሚገኙት የአዳማ አንድ እና ሁለት እንዲሁም አሸጎዳ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች በተጨማሪ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ እየገቡ መሆናቸው ይታወቃል።
በዚህም የአይሻ-2 እና የአሰላ ነፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ወደ ሥራ መግባታቸው ይታወሳል።
ይህም ሥራ ከፍተኛ የንፋስ ኃይል ማመንጨት አቅም ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት አንዷ የሆነችውን ኢትዮጵያ ሙሉ አቅሟን እንድትጠቀም የሚያግዝ ነው።
በፀሐይ ኃይል ማመንጫ ዘርፍ ደግሞ አብዛኛውን ወራት የፀሐይ ብርሃን የምታገኘው ኢትዮጵያ÷ ይህንን የተፈጥሮ ጸጋ ለመጠቀም በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
እንዲሁም በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሶላር ኃይል ማመንጫ ምርት ጋር በተያያዘ 13 ነጥብ 5 ጊጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችል የሶላር ምርት እየተመረተ ይገኛል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የምትከተለው የአረንጓዴ ኢነርጂ ልማት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅር ከማጠናከር ባለፈ ለአፍሪካ የአረንጓዴ ልማት አርዓያ እንድትሆን በማስቻል ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም እንቅስቃሴ ከሌሎች ሀገራት ጥገኝነት የተላቀቀ የኃይል ባለቤት እንድትሆን ያስችላታል።
በዮናስ ጌትነት