ዓለምአቀፋዊ ዜና

ኢራን በጦርነቱ ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን የበረራ አገልግሎት አስጀመረች

By Mikias Ayele

April 25, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢራን ከአሜሪካ እና እስራኤል ጋር በገባችበት ጦርነት ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን የበረራ አገልግሎት አስጀምራለች፡፡

በዛሬው ዕለትም በቴህራን የሚገኘው ኢማም ኾሚኒ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከሁለት ወራት በኋላ የመጀመሪያውን በረራ ወደ ቱርክ ኢስታንቡል፣ ኦማን ሙስካት እና ወደ ሳዑዲ አረቢያ መዲና ከተሞች አድርጓል ነው የተባለው፡፡

በኢራን እና አሜሪካ መካከል የተደረሰውን ጊዜያው የተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎ ቀደም ሲል ኢራን የአየር ክልሏን በከፊል ክፍት ማድረጓ ይታወሳል።

እንደ አሽራቅ ኒውስ ዘገባ፤ ኢራን በረራውን ያስቀጠለችው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አባስ አራግቺ ከፓኪስታኑ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል አሺም ሙኒር ጋር ትናንት ምሽት ተገናኝተው ለሁለተኛ ጊዜ ከመከሩ በኋላ ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም አባስ አራግቺ ከፓኪስታን ፕሬዚዳንት ሻባዝ ሻሪፍ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢሳቅ ዳር ጋር ተገናኝተው ከአሜሪካ ጋር ሁለተኛ ዙር ውይይት ሊካሄድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክሩ ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ በአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማች በሆኑት ያሬድ ኩሽነር የተመራ ልዑክ ወደ ፓኪስታን ኢስላማባድ ያቀናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሚኪያስ አየለ