የሀገር ውስጥ ዜና

 ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ …

By Mikias Ayele

April 25, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ማመንጫዎች ላይ ከፍተኛ ሥራ እየሠራች ነው።

ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማስፋፋት ከ95 በመቶ በላይ ንፁህ ኃይል የማመንጨት ተግባር እየከወነች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኦኮኖሚ ለመገንባት ቁርጠኛ አቋም ይዛ ያላትን ሰፊ የታዳሽ ኃይል አቅም በመጠቀምና በወሳኝ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር የካርቦን ልቀትን በመቀነስ ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሸጋገር የምታደርገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ ደርሷል።

ተደራሽነት ውስንነት፣ የመሠረተ ልማት ክፍተቶች እና የገበያ ተደራሽነት እጥረትን ጨምሮ ያሉ እንቅፋቶችን ለመፍታትም ባለድርሻዎችን ያቀናጀ ውጤታማ ስራ በመሰራት ላይ መሆኑ ይታወቃል።

በተለይም የነዳጅ ጥገኝነት ለመቀነስ እና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የታዳሽ ኃይልን መጠቀም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆኗል።

በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ምክንያት የተፈጠረው ችግር በነዳጅ ጥገኝነት ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ግንባታ አዋጭነትን ጥያቄ ውስጥ ከመክተቱ አስቀድሞ ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል አማራጭን ማማተርና ለውጤታማነት ብዙ ሰርታለች።

የነዳጅ ዋጋ በየጊዜው መጨመር እና ለማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱ ታዳሽ ኃይል ላይ ለመስራት የፈጠረው ዕድል የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በመጠቀም ለነዳጅ የሚወጣውን ወጪ መቀነስ የሚያስችል መንገድ ከፍቷል።

በመሆኑም አማራጭ የታዳሽ ኃይል ምንጮችን እና የተፈጥሮ ጸጋዎችን መጠቀም ትኩረት አግኝቷል።

ከአማራጭ የታዳሽ ኃይል ምንጮች የንፋስ ኃይል አንዱ በመሆኑ የኢትዮጵያን አቅም ለመጠቀም የተጀመረው እንቅስቃሴ ውጤት እያስገኘ መምጣቱን በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመረቀው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አንድ ማሳያ ነው።

ፕሮጀክቱ 100 ሜጋዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን የንፋስ ኃይል ማመንጫ የደረሰበትን የመጨረሻውን ቴክኖሎጂ ታጥቋል።