የሀገር ውስጥ ዜና

በበጀት ዓመቱ በእቅድ ከተያዙ ተግባራት 96 በመቶ መፈፀም ተችሏል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By Hailemaryam Tegegn

April 26, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበጀት ዓመቱ በእቅድ ከተያዙ ተግባራት 96 በመቶ መፈጸም ተችሏል አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የ9 ወራት አፈፃፀም ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ሲሆን፥ በመድረኩ በጥብቅ ክትትል የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም በቀሪ ወራት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

ያልተመለሱ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ምላሽ መስጠት፣ የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ ችግሮችን በመቀነስ የዋጋ ንረትን እና የገበያ ማዛባት ችግሮችን መከላከል ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ነው የገለጹት፡፡

በመሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል የመንግስት አገልግሎት የተጀመሩ ውጤታማ ስራዎችን በቀሪ ወራት ለማጠናቀቅና ቀሪ አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ አድርጎ ወደ መሶብ ለማስገባት በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡

በዚህ ዓመት መጠናቀቅ ያለባቸውን ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት ማጠናቀቅ የአፈጻጸም ግምገማ ማዕከላችን ይሆናሉ ብለዋል።

ባለፋት አምስት ዓመታት የእቅድ አፈጻጸሙ ከ90 በመቶ በላይ እያደገ መምጣቱን አስታውሰው፥ በዚህ በጀት ዓመት 96 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

ይህንን የመፈፀም ልምድ አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እንገመግማለን ያሉት ከንቲባዋ፥ ጉድለቶችን በመሙላት በቀሪዎች ወራት የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ነፃ፣ ተዓማኒና ገለልተኛ ሆኖ እንዲከናወን ሁሉም አመራር የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ አቅጣጫ አስቀምጠናል ብለዋል።