ቴክ

በኢትዮጵያ አስተማማኝ የዲጂታል ሥነ ምህዳር መገንባት የሚያስችል መሰረት ተጥሏል – በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

By Melaku Gedif

April 26, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ አስተማማኝ የዲጂታል ሥነ ምህዳር መገንባት የሚያስችል መሰረት ተጥሏል አሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፡፡

8ኛው የአፍሪካ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ፎረም በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ÷ የአፍሪካ አህጉር የወደፊት እጣ ፈንታ በእውቀት እና ትብብር ላይ መመስረት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

ፎረሙ የንግግር ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን ትራንስፎርሜሽን በተግባር ለመገንባት የሚያስችል ወሳኝ መድረክ መሆኑን አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎትና በጤና ፈጠራ ረገድ እያከናወነች ላለው ተግባር በተባበሩት መንግሥታት እውቅና ማግኘቷን አስታውሰዋል፡፡

ይህም የቴክኖሎጂ አቅም ሕይወትን ለመታደግና ጠንካራ ማሕበረሰብ ለመገንባት ያለውን ፋይዳ የሚያረጋግጥ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ራዕይን በማዘጋጀት ከባህላዊ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ የምታደርገውን ሽግግር በፖሊሲና በስትራቴጂ እየመራች ሲሆን ÷ ሒደቱም አካታችነትንና ጽናትን ማዕከል ያደረገ ነው ብለዋል።

የፈጠራ ሥራዎችን ለማበረታታትና የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ጠንካራ ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፎች መዘርጋታቸውን ጠቁመው ÷ አስተማማኝ የዲጂታል ሥነ ምህዳር መገንባት የሚያስችል መሰረት መጣሉን ተናግረዋል።

የዲጂታል መሰረተ ልማት መስፋፋት፣ የብሔራዊ መለያ አቅርቦትና የመንግስት አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ የማዘመን ሥራዎች የዜጎችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጣቸው ባለፈ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን እምነት እያጠናከሩ ይገኛሉ ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ተንቀሳቃሽነትና በአረንጓዴ ልማት እያከናወነች ያለችው ተግባር የኢኮኖሚ እድገትና የአካባቢ ጥበቃ ተጣጥመው መሄድ እንደሚችሉ የሚያሳይ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

በሰው ሰራሽ አስተውሎትና በኒውክሌር ሳይንስ ሰላማዊ አተገባበር ላይ የምታደርገው ኢንቨስትመንት ተስፋ ሰጭ ነው ማለታቸውንም የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ አለምነው ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ሀገራት በሳይንስ ዲፕሎማሲ ተቀናጅተው በመስራት በቴክኖሎጂው ዘርፍ እንደ ተሳፋሪ ሳይሆን እንደ መሪና አርክቴክት ሊሳተፉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡