አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው የመኸር እርሻ የምግብ ዋስትናን ለሚያረጋግጡ የግብርና ምርቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል አለ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ።
የቢሮው ሃላፊ አቶ አንድሪው ቱት እንዳሉት÷ በክልሉ በ2018/19 የመኸር ምርት ከ180 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ5 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡
በመኸር እርሻው የምግብ ዋስትናን ለሚያረጋግጡ የግብርና ምርቶች ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል፡፡
የበቆሎ ምርት በዋናነት የምግብ ዋስትናን ከሚያረጋግጡ የግብርና ውጤቶች መካከል እንደሚመደብ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ሩዝና ሌሎች የጓሮ አትክልቶችም ትኩረት ተሰጥቶ ከሚሰራባቸው መካከል እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
ስለሆነም በምርት ዘመኑ የታቀደውን መሬት ለማልማት በሶስቱም ዞኖች የእርሻ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡
ዕቅዱን ለማሳካት ሁሉም ማሳዎች በዘር ይሸፈናሉ የሚል ግብ ተቀምጦ ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የመኸር እርሻ ልማቱን ውጤታማ ለማድረግ የግብርና ግብዓት ሥርጭት እየተከናወነ መሆኑንና ለዚህም ለአመራሮችና ባለሙያዎች ስምሪት እንደሰተጠ መናገራቸውን ቢሮው ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡